አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የ“ጽዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ አካል የሆነው የጽዱ ጤና ተቋማት ንቅናቄ ዛሬ ተጀምሯል፡፡
ጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ጽዳትና ንፅህናን ለማሻሻል ያለመ የጽዱ ኢትዮጵያ ጽዱ ጤና ተቋማት ንቅናቄ ”የጽዱ ኢትዮጵያ ጽዱ ጤና ተቋማት ለተሟላ ጤንነት ” በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በቅዱስ ጴጥሮስ እና በአለርት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች አስጀምሯል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መካሄድ የጀመረው ንቅናቄ ሆስፒታሎችን ንፁህ በማድረግ ኅብረተሰቡን ጤናማ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የጽዱ ጤና ተቋማት ንቅናቄ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ዛሬ በሁለት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች የተጀመረውን ንቅናቄም በያገባኛል እናይገባኛል ስሜት በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በበረከት ተካልኝ