Fana: At a Speed of Life!

ሐረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል- ቢሮው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐረር ከተማንተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የክልሉን ባህል ፣ ቅርስና ቱሪዝም ከማስተዋወቅ አንጻር ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ከተማዋ ሙዚዬሞችን ያቀፈች ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም ሎጎ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን ነው ያስረዱት፡፡

በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ልማት ሥራዎች በአካባቢው ያለውን ተፈጥሯዊ ሥነ-ምህዳር በመጠቀም ታሪክ፣ ባህልና እሴትን በጠበቀ መልኩ መሰራቱን ጠቁመዋል።

የቱሪስት ልማት ሥራው የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ እና ከክልሉ መንግስት በተመደበ በጀት የሐረር ኢኮ ፓርክ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸው ÷ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ክልሉን የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል።

የሸዋል ዒድ በዓልን በዩኔስኮ ማስመዝገብ መቻሉን የገለጹት ኃላፊው÷ ዘንድሮም በዓሉ ባማረና በደመቀ መልኩ መከበር መቻሉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የህዝብን አብሮነትና አንድነትን የሚያጎለብቱ እንዲሁም ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ስራዎች እንደተከናወኑ ማንሳታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው 5 ባህላዊ ቤቶች እና 4 ጥንታዊ አድባራት ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ የማደስ ስራ መሰራቱን ጠቁመው÷ በተለይም የሱቅጣጥ በሪ ታሪካዊ በር እድሳት እና የራምቦ ሙዚዬም እድሳት ተግባር እየተገባደደ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ2015 ዓ.ም ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ባለፉት 9 ወራት ክልሉን የጎበኙ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 100 በመቶ እንዲሁም የውጪ ቱሪስቶች 6 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አክለዋል።

በዘርፉም የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲጎለብትም እየተደረጉ ርብርቦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት ሃላፊው÷ የክልሉ ነዋሪም ቅርስን በመጠበቅና እየተሰሩ በሚገኙ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ተግባራት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.