Fana: At a Speed of Life!

ስራ ፈጠራን በማበረታታት የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስራ ፈጠራን በማበረታታትና የተረጂነት አመለካከትን በመቀየር የምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኋላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እንደቀጠለ ነው።

መድረኩ ሶስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት፣ ከስራ ዕድል ፈጠራ እና የተረጂነት አመለካከትን ከመለወጥ አኳያ በተሰሩት ስራዎች ዙሪይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

በውይይቱም ፓርቲው በሱፐርቪዢን ምልከታ እና በሌሎችም ጊዜያት በተደረጉ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

ለአብነትም የምርት አቅርቦትን ከማሻሻል፣ የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋትና የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠር አንጻር የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች እያስገኙ መሆኑ ተመላክቷል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኋላፊ አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት፤ ህዝቡን እየጎዳ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በመንግሥት እና በፓርቲ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የተረጂነት አመለካከትን ከመቀየር አኳያም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ የመስራት አቅም ያላቸው ዜጎች ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ ለማድረግ በቀጣይም በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

የምግብ ዋስትናን እና የኢኮኖሚ ነጻነትን ማረጋገጥ መቻል የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትልቅ አቅም መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም የተለያዩ ኢንሼቲቮች ተቀርጸው ወደ ምርት መግባታቸውን ጠቁመው በዚህም የምርት አቅርቦት እያደገ መምጣቱን መናገራቸውን የፓርቲው መረጃ አመላክቷል።

የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋትና የስራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የታዩ ጉድለቶችን በመፍታት ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንደሚገባም ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.