በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ዛሬ ተጠባቂ ጨዋታ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ምሽት በሚካሄደው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ከባየርን ሙኒክ ይፋለማሉ፡፡
ጨዋታው ከምሽቱ 4:00 ጀምሮ በባየር ሙኒክ ሜዳ አሊያንዝ አሬና ሲካሄድ፤ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ቀጣይ ሳምንት በሪያል ማድሪድ ሜዳ ሳንትያጎ ቤርናባው ይካሄዳል።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 26 ጊዜ ተገናኝተው የተጫወቱ ሲሆን የጀርመኑ ክለብ 12 ጊዜ በማሸነፍ የተሻለ ክብረወሠን አለው።
በአንፃሩ የስፔኑ ግዙፍ ክለብ ሪያል ማድሪድ 11 ጊዜ ሲያሸንፍ ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታወች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
ነገር ግን በፈረንጆቹ 2014፣ 2017 እና 2018 ከሜዳው ውጭ ወደባቫሪያ ተጉዞ ያደረጋቸውን ሶስት ተከታታይ ግጥሚያወች በማሸነፍ ሪያል ማድሪድ የበላይነት አለው።
ከሁለት ሳምንት በፊት በሩብ ፍፃሜው በተካሄዱ ጨዋታዎች ባየርን ሙኒክ አርሰናልን እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ማንቼስተር ሲቲን በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡