በስንዴ ምርት ላይ የታየው ስኬት በአትክልትና ፍራፍሬም ሊደገም ይገባል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስንዴ ምርት ላይ የታየው ስኬት በአትክልትና ፍራፍሬም ሊደገም እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በመልካሳ ምርምር ማዕከል በአትክልትና ፍራፍሬና በሜካናይዜሽን እየተሰሩ ያሉ የምርምር ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ፥ በስንዴ ላይ የታየው ስኬት በአትክልትና ፍራፍሬ ሊደገም ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
መልካሳ ግብርና ምርምር እንደሀገር በአትክልትና ፍራፍሬ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ቴክኖሎጂ ማፍለቅ ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ÷ በምርምር ማዕከላት የተገኙ ምርምሮችን በማባዛት ለአርሶአደሩ ተደራሽ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
በመሆኑም የፍራፍሬ ዝርያን በማሻሻል የምግብ ዋስትናችን ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂዎች ምርምር ላይ ተወስነው መቅረት የለባቸውም ነው ያሉት፡፡
ግብርናን ካለቴክኖሎጂ ማዘመንና ማሻገር ስለማይቻል የምርምር ማዕከላት ቴክኖሎጂዎችን እንዲያሻሽሉ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ከሚኒስቴሩ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት ÷ የምርምር ማዕከላት ቴክኖሎጂ የማፍለቅ፣ ማስተዋወቅ፣ ተደራሽ ማድረግና የአቅም ግንባታ ስራዎችን እየሰሩ ነው።
መልካሳ ግብርና ምርምር በፍራፍሬ ልማት ረገድ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።