የህይዎትን መልክ ስለሚገልጹ መጽሐፍት
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)መጽሐፍት ጓደኞች ናቸው ይላሉ ብዙዎች፡፡ ምን ማለታቸው ይሆን ብዬ ላሰማኋቸው ጥያቄዎች መልሱ ብቸኝነትን ማስታገሻ፣ እይታን ማስፋት እንዲሁም ከምናውቀው ውጪ ያለን ዓለም አመላካች መስታዎት ናቸው፡፡
ዛሬ (በፈረንጆቹ ሚያዝያ 23) የሚከበረው የዓለም መጽሐፍ እና የቅጂ መብት ቀን በመጻሕፍትና ማንበብ የሚሰማን ደስታ ለማጋራትና ለመግለጽ የሚከበር በዓል ነው።
በዓሉ ለመጽሐፍ ይህ ቀን ብቻ ነው ያለህ ብሎ ለመሰየም ሳይሆን መጽሐፍ ህይዎታችን ውስጥ ያለውን አስተዋጽኦ አስበንበት ተወያይተንበት ይበልጥ የምንማርበት ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታና የትም ብንሆን የምንኮራባቸው አባቶቻችን ብራና ፍቀው ቀለም በጥብጠው እውቀትን ለእኛ ነጋቸው ለማውረስ የሄዱበት መንገድ ሩቅ ነው፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን በጊዜው ለማሰብ የማይሞከረውን የሣይንስ፣ የሥነ ከዋክብት፣ የህክምና እና የተለያዩ ረቂቅ መረጃዎች በጽሁፍ አልያም በምስል መቀመጥ አለበት በሚል ተሰድረው አስቀምጠዋል፡፡
ሆኖም እነዚህን መጽሐፍ ተጠቅመንባቸዋል ወይ የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው፡፡
ምክንያቱም አንድ መጽሐፍ ሲጻፍ መረጃን ሰድሮ ማስቀመጡ ሣይሆን ወይም መረጃውኮ አለ ማለቱ ሣይሆን ከመረጃው በመነሳት ህይዎት ላይ ለውጥ መፍጠር ነው፡፡
ብዙ ሰዎች መጽሐፍ አነበብኩ ሲሉ እንሰማለን ፤ ይህ መጽሐፍ ህይዎቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አስገኝቶልኛል ፤ ይህን ችግሬን እንድቀርፍ ምክንያት ሆኖልኛል ሲባል በአብዛኛው አይሰማም፡፡
ለምን ለሚለው ጥያቄም መጽሐፍን እና ንባብን ከምንረዳበት ጽንሰ ሃሳብ ይጀምራል፡፡
አንድ ሰው ገጠመኙን በመጽሐፍ ሲሰድር ከራሱ ሃሳብ እና አረዳድ እንዲሁም ገጠመኝ ተነስቶ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡
ይህ አረዳድ ተደራሲው ጋር ሲደርስ የህይዎት መልክን በሌላ መልኩ የሚያሳይ ወይም አጉልቶ የሚያቀርብ ሊሆንለት እንደሚገባ ይታመናል፡፡
አንድ ታሪክ በመጽሐፍና በፊልም ሲቀርብ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ይታወቃል፡፡
ታሪኩ በፊልም የቀረበ እንደሆን ተደራሲው የራሱን ምስል ሳይሆን ፊልሙ በቀደደለትን ምስል በመመልከት ቀጥሎ የሚከሰተውን እየገመተ ይቆያል፡፡ ሆኖም መጽሐፍ ተደራሲው ላይ ምናባዊ እይታን ለመፍጠር ሁኔታዎችን ምስል ባዘሉ ቃላት መግለጽ ይጠበቅበታል፡፡
ይህም የአንባቢን እይታ የሚያሰፋ እና ምናባዊ እይታን የሚያሰፋ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
ሆኖም በአሁኑ ወቅት የማህበራዊ ሚዲያ ቀድሞም በቋፍ ላይ ያለውን የንባብ ባህል እየገደለው ነው ሲባል ይሰማል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያ ደግሞ በአብዛኛው አጠር ያለ ነገርን በማስለመዱ ምክንያትና ቀላልም ከመሆኑ አንጻር መጽሐፍ ገዝቶ፣ ልቦናን ሰብስቦ፣ ትዕግስት አድርጎ ለማንበብ ፈታኝ ወቅት ነው ይባላል፡፡
በዚህም በተለይ ማንበብ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መረጃን በማግኘት የህይዎትን ቋጠሮ የሚፈታ እንደሆነ ከህጻናት ጀምሮ ባሉ የእድሜ እርከኖች ማሳወቅና ንቅናቄ መፍጠር ይገባል፡፡
በዚህም በትምህርት ቤቶች፣ ሻይ ቡና በምንጠቀምባቸው ስፍራዎች፣ በተቋማት፣ በማዕከላትና በተለያዩ ስፍራዎች መጽሐፍን ማግኘት የሚቻሉባቸውን መንግዶች መፍጠር ፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ለመጽሐፍት ሚሰጡትን ቦታ ማሳየትና በተግባር መግለጽ ፤ ደራሲያንን ማበረታታት እና የመሳሰሉትን እንደንቅናቄ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
በመሰረት አወቀቀ