Fana: At a Speed of Life!

ናይጄሪያዊው ለ60 ተከታታይ ሰዓታት ቼስ በመጫወት አዲስ ክብረወሰን አስመዘገበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጊነስ ወርልድ ሪከርድ ክብረወሰን ለመስበር ያለመው ናይጄሪያዊ የቼስ ተጫዋች ለ60 ተከታታይ ሰዓታት በመጫወት ህልሙን ማሳካቱ ተገልጿል፡፡

ከአሜሪካዊው የቼስ ሻምፒዮን ሻወን ማርቲኔዝ ጋር በኒው ዮርክ ታይምስ አደባባይ ለ60 ሰዓታት የተጫወተው ናይጄሪያዊው ቱንዴ ኦናኮያ እያንዳንዱን ጨዋታ በማሸነፍ ማጠናቀቁም ተነግሯል፡፡

እስከ አሁን በቼስ ጨዋታ በጊነስ ወርልድ ሪከርድ የተመዘገበው ረጅሙ ሰኣት 56 ሰዓት ከ9 ደቂቃ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ይሁንና መዝገቡን የሚይዘው ድርጅት የባለቤትነት መብትን ለመስጠት ለ60 ሰዓታት በመጫወት ክብረወሰን ለመስበር የተደረገውን ሙከራ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ እንደሚወስን ተጠቁሟል።

ክብረወሰን የመስበር ሙከራውም በአፍሪካ የቼስ ስፖርትን ለማስፋፋት 1 ሚሊየን ዶላር ለማሰባሰብ ያለመ ነው ተብሏል።

እንዲሁም በኦናኮያ በተቋቋመው በጎ አድራጎት ድርጅት በአህጉሪቱ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አካባቢዎች ትምህርትን ለማስተዋወቅ እንደሚውልም መመላከቱን ዩፒአይ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.