ኢትዮጵያ በማንዴላ ዋንጫ የአፍሪካ ቦክስ ውድድር ባስመዘገበችው ድል ኤምባሲው ደስታውን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በማንዴላ ዋንጫ የአፍሪካ ቦክስ ውድድር ባስመዘገበችው ድል በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደስታውን ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በደርባን በተካሄደው የቦክስ ውድድር ላይ ሦስት የብር እና ሦስት የነሐስ በድምሩ ስድስት ሜዳሊያ አግኝታለች፡፡
አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ሁሉንም ተወዳዳሪዎችና የልዑካን ቡድን አመራሮች በውድድሩ ስፍራ ተገኝተው ማበረታታታቸውም ነው የተነገረው፡፡
ውጤቱም በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ ኢትዮጵያ ትልቅ እምቅ አቅም እንዳላት ያመላከተ አኩሪ ድል መሆኑን በመጠቆም የተገኘው ድልም እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
ልዑኩ በተሳትፎው ሰፊ ልምድ ያገኘበትና ለቀጣይ የተጠናከረ ተሳትፎ መነሳሳት እንደሚፈጥርለትም ያላቸውን እምነት ጠቅሰዋል፡፡
ኤምባሲው በደርባንና በአካባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች እና ወዳጆች በስታዲየሙ በመገኘት ለተወዳዳሪዎቻችንን ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ባቀረበው ጥሪ መነሻ በርካታ የዳያስፖራ አባላት በውድድሩ ስፍራ መገኘታቸውም ተነስቷል፡፡
በዚህም ከፍተኛ ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን ለዚህም ኤምባሲው የላቀ ምስጋና አቅርቧል።
አምባሳደር ሙክታር (ዶ/ር) በፍጻሜው ውድድሩ ላይ የተገኙትን የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የደቡብ አፍሪካ የስፖርት ሚኒስትርን ጨምሮ የኮንፌዴሬሽኑን ከፍተኛ አመራሮች በማግኘት በስፖርቱና ተያያዥ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብ መለዋወጣቸውን የኤምባሲው መረጃ አመላክቷል።