Fana: At a Speed of Life!

የስኳር ህመም አይነቶች እና ምልክቶች

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የስኳር ህመም በደም ውስጥ የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ሆኖ በሚገኝበት ሰዓት የሚከሰት ተላላፊ ያልሆነ የህመም አይነት ነው።

በዋናነት አራት የስኳር ህመም አይነቶች አሉ፤ እነርሱም አይነት አንድ፣ አይነት ሁለት፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰትና በሌሎች ተዛማች ህመሞች የሚመጣ የስኳር ህመም ናቸው።

ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ (አይነት አንድ፣ አይነት ሁለት) ዋና የስኳር አይነቶች ሲሆኑ÷ አይነት አንድ የሚባለው ኢንሱሊን የሚያመነጨው በተለምዶ ቆሽት የሚባለው የሰውነታችን ክፍል ኢንሱሊን ማመንጨት ሲያቆም ነው።

ይህ ችግር በዋናነት የሚመጣው የሰውነት የህመም መከላከያ ሥርዓት ያለአግባብ ቆሽት ላይ ጥቃት ሲያሳድር የሚከሰት የስኳር ህመም ሲሆን÷ በተለምዶ ህጻናትና እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው።

አይነት ሁለት የሚባለው ደግሞ በአካባቢ ተጽዕኖዎች ማለትም ጤናማ ባልሆነ የአመጋገብ ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤ፣ ከልክ በላይ በሆነ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው።

በእነዚህ አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት ቆሽት ተገቢውን ሥራ ለመከወን ይሳነዋል፤ አብዛኛው ወይም 90 በመቶ የስኳር ህመም አይነት ሁለት ውስጥ የሚካተት ነው።

ሌላው በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው የስኳር አይነት ሲሆን÷ ብዙ ጊዜ ከእርግዝና ሆርሞኖች ጋር ተያይዞ የሚመጣ የስኳር አይነት ነው፤ በእርግዝና ጊዜ ይከሰታል፤ ልክ እርግዝናው ሲያልፍ ይጠፋል ወይም መታየቱን ያቆማል።

ከተዛማጅ ህመሞች ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የስኳር አይነት ደግሞ÷ የእንቅርትን የመሳሰሉ የሆርሞን ችግሮችና የተለያዩ በሽታዎች ስኳርን ሊያመጡ ይችላሉ፤ ተዛማጅ ህመሞች በሚታከሙበት ወቅት ስኳሩም አብሮ የመጥፋት ሁኔታ አለ።

ሌላው የተወሰኑ መድሃኒቶች ለስኳር ህመም መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን፤ ይህ ችግር ከተዛማች ህመሞች ጋር ተያይዞ ከሚመጣው የስኳር አይነት የሚመደብና ምልክቱ ሲታይ መድሃኒቶችን መቀየር ስኳሩን ሊያጠፋው ይችላል።

የስኳር ህመም አጋላጭ መንስኤዎች በሁለት ሲከፈሉ፤ እነሱም በቤተሰብ ወይም በዘር የሚተላለፍ እና በአካባቢያዊ ተጽኖዎች የሚከሰት የስኳር ህመም መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህም ሲባል ጤነኛ ካልሆነ የአመጋገብ ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤ፣ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረግ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት ወዘተ ጋር ተያይዞ የስኳር ህመም ይከሰታል ወይም ተጋላጭነትን ይጨምራል።

ሁሉም የስኳር አይነቶች በተወሰነ መልኩ ምልክታቸው ተመሳሳይነት ሲኖረው፤ ከወትሮው በተለየ የውሃ መጥማት፣ የሽንት መጠን መጨመር፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ ድካም፣ አንዳንድ ጊዜ የእንቅልፍ መዛባቶች፣ በተለያዩ ኢንፌክሽኖች መጠቃት ሁኔታዎች ወይም የበሽታ መከላከል አቅም መቀነስ ስሜቶች ይከሰታሉ።

ነገር ግን ሁሉም የስኳር ተጠቂዎች እነዚህን ምልክቶች ላያሳዩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ምንም ምልክት ሳያሳይ፤ እንደ አጋጣሚ በሚደረግ የጤና ምርመራ ላይ የስኳር መጠኑ ከፍ ብሎ ወይም የስኳር ተጠቂ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።

የስኳር መጠንን የማይጨምሩ ምግቦችን መውሰድ፣ በተቃራኒው ደግሞ የፋብሪካና ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችንና ምርቶችን ከገበታችን ማውጣት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጤናማ ፕሮቲኖችንና የቅባት ምግቦችን አካቶና አመጣጥኖ መመገብ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ (ከሀኪም ጋር ተነጋግሮ)፣ በሃኪሞች የሚታዘዙ መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፣ በስኳር አማካኝነት የሚመጡ ተዛማጅ ህመሞች እንዳይከሰቱ ቀድሞ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.