በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማመጣጠን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በክልሉ ከተሞች የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ቢሮው በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የፌዴራል 1320/2016 የመኖሪያ ቤት የአከራይና ተከራይ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሆሳዕና ከተማ እየመከረ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል በወቅቱ እንዳሉት÷ የቤት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማመጣጠን የተለያዩ ስልቶች ተነድፈው እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
የመኖሪያ ቤት እጥረቱን ለመፍታት የክልሉ መንግስት የማህበር ቤቶችን የማስፋፋት፣ የበጎ ፈቃድ ቤቶች ግንባታን የማበረታታት፣ የቁጠባ ቤቶችንና የሪልስቴት ግንባታ አማራጮችን የማዘጋጀት ስራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አዲሱ አዋጅ በክልሉ በሚገኙ ስድስት ከተሞች እንደሚተገበር የገለጹት አቶ ስንታየሁ፤ አዋጁ የንግድ ተቋማትን እንደማይመለከት መግለጻቸውን ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም አዋጁ በአከራይና ተከራይ መካከል ጤናማና ህጋዊ ግንኙነትን የሚያረጋግጥና ያሉትን ቤቶች በፍትሀዊነት ለመጠቀም የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።