የበልግ ዝናብ የሚያስከትለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እየሰራሁ ነው -ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የበልግ ዝናብ የሚያስከትለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የፌደራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
ኮሚሽነሩ አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም (ዶ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷በኮሚሽኑ ትንበያ 2 ሚሊየን ዜጎች በጎርፍ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል እና 1ሚሊየን ዜጎች ደግሞ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡
ይህንን ተከትሎም በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በኩል ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ሽፈራው ተ/ማርያም (ዶ/ር) ተናግረዋል ፡፡
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለጎርፍ መከላከያ የሚሆን የመከለያ ግንባታ መከናወኑን ጠቅሰው በሌሎች አካባቢዎችም ይሄው ተግባር እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል ፡፡
በጎርፍ ምክንያት መንገዶች ሲዘጉ የሚያጋጥመውን ችግር ለመፍታትም ግብዓቶችን ቀድሞ የማከማቸት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል ፡፡
በመሳፍንት እያዩ