በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ባለው ክፍል በ2024 የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ይመዘገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ባለው ክፍል በፈረንጆቹ 2024 ካለፈው ዓመት የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም ባንክ ገለጸ።
ባንኩ አዲስ ባወጣው ሪፖርት በጥናቱ የደረሰበትን ቅድመ-ግምት ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱም በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከሰሃራ በታች የሚገኘው የአፍሪካ ክፍል የ3 ነጥብ 4 በመቶ አማካይ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሏል።
በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ይበልጥ ከፍ ብሎ የ3 ነጥብ 8 በመቶ አማካይ ዕድገት እንደሚኖረው ይጠበቃል ተብሏል።
ባለፈው ዓመት በአካባቢው የተመዘገበው አማካይ ዓመታዊ ዕድገት 2 ነጥብ 4 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ በተጠቀሰው ቅድመ ግምት መሠረት ዘንድሮ የተሻለ የኢኮኖሚ መነቃቃትና ዕድገት ይመዘገባል ነው የተባለው።
የዓለም ባንክ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ መሻሻልም በዋነኛነት በተጠቀሰው የአፍሪካ ክፍል የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ ስለሚሄድና ይህንንም ተከትሎ የነፍስ-ወከፍ ገቢና የመግዛት አቅም ስለሚጨምር ነው ብሏል።
ባንኩ አያይዞም ዘንድሮና በተከታዩ ዓመት የዋጋ ግሽበቱ እየሰከነ የሚሄድባቸው ምክንያቶች እንዳሉም አንስቷል።
ይህም ዓለም ዓቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ቀስ በቀስ እየተስተካከለ በመሄድ ላይ መሆኑና የሸቀጦች ዋጋ በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑ እንደሚጠቀሱ ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም መንግስታት ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ የገንዘብና የፊስካል አሰራሮቻቸውን ጥብቅ እያደረጉ በመሆናቸው እንደሆነም አመላክቷል።