አቶ አረጋ ከበደ የክልሉ ሕዝብ ላደረገው ድጋፍና ለሰላም መስፈን ላሳየው ቁርጠኝነት አመሰገኑ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ ሕዝብ ላሳየው ድጋፍ እና ለሰላም መስፈን ላሳየው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አቶ አረጋ በዛሬው ዕለት በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎቸ ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
ሰላም ወዳዱና በችግሮችም ውስጥ ሆኖ የነገዎቹን ዕድሎችና መልካም ፍሬዎች በአስተውሎት የመተንበይ ችሎታ ያለው የክልሉ ህዝብ ያጋጠሙትን ውስጣዊ ችግሮች ተቋቁሞ አደባባይ በመውጣት ለሰላም መስፈንና ለመንግስት ያለውን ጥልቅ ድጋፍ ገልጿል ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ በችግር አረንቋ ሳይዋጥ እና በሴረኞች ሳይደናገር ለመንግስት ላደረገው ድጋፍና ለሰላም መስፈን ላሳየው ቁርጠኝነትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች እና የፀጥታ አካላት ሰልፍን በማስተባበርና ፀጥታውን በማስከበር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ማመስገናቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡