የቻይናው ሲኢኢሲ ኩባንያ በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች መሰማራት እፈልጋለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ኢነርጂ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሲኢኢሲ) ኩባንያ በአዳዲስ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንዲሁም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር መስራት እንደሚፈልግ ገለጸ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ከኩባንያውን ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የኩባንያው ኃላፊዎችም በውይይቱ ላይ አዳዲስ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት፣ የግንባታ ግብዓቶችን እና የኤሌክትሪካል ቁሶችን በማምረት እንዲሁም በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ያላቸውን እቅድ አቅርበዋል።
አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው ከኩባንያው ጋር በጋራ ለመስራት ኮርፖሬሽኑ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ወደ ቀጣይ የቅድመ ኢንቨስትመንት ዝግጅት ምዕራፍ ለመሸጋገርም ስራዎች እንዲጀመሩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተቀማጭነቱን ቻይና ያደረገው ሲኢኢሲ ኩባንያ÷ ከቻይና ውጪ በ140 ሀገራት ፕሮጀክቶችና ከ130 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን ከ60 ቢሊየን ዶላር በላይ ተቀማጭ ትርፍ እንዳለውም ተመላክቷል፡፡