ኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት ውጤታማ እንዲሆን ከፕሮጀክት ጀምሮ ሊሰራበት ይገባል – የቦክስ ስፖርተኞች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት ውጤታማ እንዲሆን ከፕሮጀክት ጀምሮ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ በ13ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታ በቦክስ ስፖርት ወርቅ ያስገኙት ስፖርተኞች ተናገሩ፡፡
የቦክስ ባለወርቆቹ ቤተልሄም ገዛኸኝ እና ቤተል ወልዴ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ ከዓመታት ቆይታ በኋላ በሴቶች የቦክስ ስፖርት የሀገራቸውን ስም በማስጠራታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
መድረኩ ለአትሌቶቹ የመጀመሪያ ዓለም አቀፋዊ ውድድር ከመሆኑ ጋር ተያይዞና በአክራ የነበረው አስቸጋሪ የአየር ጸባይ ሳይበግራቸው ተጋጣሚዎቻቸውን እንዳሸነፉ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የ2024ቱን የፓሪስ ኦሎምፒክ ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ውጤት ለማምጣት እንደሚሰሩ ነው የገለጹት፡፡
የቦክስ ስፖርት ከተሰራበት ውጤታማ የሚያደርግ የስፖርት ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው÷ይሁን እንጂ ዘርፉ በኢትዮጵያ ትኩረት እንደተነፈገው ጠቅሰዋል፡፡
ቀደም ሲል የቦክስ ስፖርት ክለቦች እና አካዳሚዎች እንደነበሩ የገለጹት ስፖርተኞቹ÷ አሁን ላይ ግን የክለቦች እና የአካዳሚዎች ቁጥር በእጅጉ መቀኑሱን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም እንደ ሀገር በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ከተፈለገ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽንን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በዘርፉ ከአካዳሚ ጀምሮ ሊሰሩበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዋጋ ከፍለው አንዳንድ ፕሮጀክቶችን የሚያሰለጥኑ የቦክስ አሰልጣኞች የቁሳቁስ ድጋፎችን ጨምሮ የልምድ ልውውጥ እና ዓለም አቀፋዊ ስልጠና ሊመቻችላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የቦክስ ዳኝነት ክፍትት መኖሩን የጠቆሙት ቦክሰኞቹ÷ የቦክስ ዳኞች ዓለም አቀፋዊ የልምድ ልውውጥ ሊያደርጉ እና ተጨማሪ ስልጠናዎችን ሊወስዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡