Fana: At a Speed of Life!

የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ምክንያቶች

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጡት ካንሰር ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ በጡት ውስጥ ያሉ ሕዋሳት አድገው እና ተከፋፍለው ዕጢ ሲፈጥሩ የሚከሰት ሕመም ነው።

የጡት ካንስር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ምክንያቶች ምንድናቸው?

– እድሜ፡- በጡት ካንሰር የመያዝ እድል በእድሜ እየጨመረ ይመጣል፤ አብዛኛዎቹ የጡት ካንሰሮች ከ35 ዓመት በኋላ ይከሰታሉ።

– የመራቢያ ታሪክ፡- የወር አበባ ጊዜያት ከ12 አመት በፊት መጀመር እና ከ55 አመት በኋላ ዘግይቶ መቆም ሴቶችን ረዘም ላለ ጊዜ ለሆርሞን ያጋልጣል፤ ይህም በጡት ካንሰር የመያዝ እድላቸውን ከፍ ያደርገዋል።

– የጡት ካንሰር የግል ታሪክ ወይም አንዳንድ ካንሰር ያልሆኑ የጡት በሽታዎች፡- የጡት ካንሰር ያለባቸው ሴቶች ለሁለተኛ ጊዜ በጡት ካንሰር የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ነው።

– የጡት ወይም የማህፀን ካንሰር የቤተሰብ ታሪክ፡- አንዲት ሴት እናት፣ እህት ወይም ሴት ልጅ (የመጀመሪያ ደረጃ ዘመድ) ከእናቷ ወይም ከአባቷ ወገን የጡት ወይም የማህፀን ካንሰር ካለባት ለጡት ካንሰር የመጋለጥ እድሏ ከፍ ያለ ነው።

– የጨረር ሕክምናን በመጠቀም ያለፈ ሕክምና፡- ከ30 ዓመታቸው በፊት በደረት ወይም በጡት ላይ የጨረር ሕክምና የወሰዱ ሴቶች በኋለኛው ሕይወታቸው በጡት ካንሰር የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

– አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከመጠን በላይ መወፈርና አልኮል መጠጣትም በጡት ካንሰር የመያዝ እድልን ከፍ ያደርጋል፡፡

– ሆርሞኖችን መውሰድ፡- በማረጥ ወቅት የሚወሰዱ አንዳንድ የሆርሞን ምትክ ሕክምና ከአምስት ዓመት በላይ ሲወሰዱ ለጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ሊጨምሩ ይችላሉ።

– የእርግዝና ታሪክ፡- ከ30 ዓመት በኋላ የመጀመሪያ እርግዝና መኖሩ፣ ጡት አለማጥባት እና መካን መሆን የጡት ካንሰርን ተጋላጭነት ሊጨምር እንደሚችል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የጡት ካንሰር ስጋትን ለመቀነስ ምን ማድረግ ይገባል?

አልኮልን መገደብ፣ ጤናማ ክብደትን መጠበቅ፣ ጡት ማጥባት፣ የወር አበባ ከቆመ በኋላ የሆርሞን ሕክምናን ለብዙ ጊዜያት አለመውሰድ የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ይጠቅማል።

የራስን ጡት በራስ የመመርመር ዘዴ፡- በወር አበባ ዑደት ምክንያት የሚመጣውን የጡት ቅርፅ፣ መጠንና ስሜት ለውጥ ለመቀነስ በየወሩ በተመሳሳይ ጊዜ የወር አበባ በመጣ ከ1 ሳምንት በኋላ በሁለቱም የጡቶቹ ጫፍ የሰረጎዱ፣ በተለየ መልኩ የቀሉ፣ ሁለቱ ጡቶች ካላቸው የተፈጥሮ ልዩነት በስተቀር ሌላ የመጠንም ሆነ የቅርፅ ልዩነትና የጓጎለ እብጠት እንዳላቸው ጡትን በእጅ በመዳሰስ ማየት ተገቢ ነው፡፡

የሚያጠራጥር ነገር ሲኖርም ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሀኪም በማማከር ተጨማሪ ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.