Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ ብልጽግና በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ተጨባጭ ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ተጨባጭ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።

የፌዴራል ተቋማት የብልጽግና ፓርቲ አባላት ማጠቃለያ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

አቶ አደም ፋራህ በኮንፈረንሱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በግማሽ የምርጫ ዘመን አፈጻጸም ዘርፈ-ብዙ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ላስመዘገባቸው ስኬቶች በርካታ መሠረቶች መኖራቸውን ገልጸው÷ የኢትዮጵያን እምቅ አቅም ለመለየትና ለመጠቀም የተደረገው ጥረት የመጀመሪያው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም በሀገር በቀል እሳቤ ሁለንተናዊ ብልጽግና የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ዕውን በመሆን ላይ ትገኛለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከብዝኃ የኢኮኖሚ ዘርፎች አኳያም በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና በሌሎች ዘርፎች ተጨባጭ ስኬቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡

ሥራዎች በውጤታማነት ተግባራዊ እንዲሆኑና ፈተናዎችን ለመመከት የተደረገው ትግል ውጤት ማስገኘቱን እና ፕሮጀክቶችን በጥራት፣ በፍጥነት እና ፈጠራ በታከለበት መልኩ ማከናወን መቻሉንም ጠቁመዋል።

የፌዴራል ተቋማት የሚሠሯቸው መሠረተ-ልማቶች ሁሉንም ባማከለ መልኩ በፍትሐዊነት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

በዚህም መላው ሕዝብ የፓርቲው አጀንዳዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ በባለቤትነት ስሜት በመሳተፍ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

በሕዝብ ንቅናቄ አመርቂ፣ ትውልድ ተሻጋሪ እና የብልጽግና ዐሻራ የሆኑ ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

ፓርቲው በኑሮ ውድነት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በፀጥታ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች መሥራቱንና ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የሠላም ችግሮችን ለመፍታት በተደረገው ጥረትም የኢትዮጵያን ኅልውና ማስከበርና ማስቀጠል ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የመንግሥትን ሥልጣን በኃይል መያዝ እንደማይቻል መረጋገጡን ጠቁመው÷ ሥልጣን በሐሳብ ልዕልና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ እንደሚገኝ የሠላም ችግሮችን ለመፍታት የተደረገው ጥረት በሚገባ ማስረዳቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ የችግር ምንጭ በመሆን ላይ የሚገኙ አካላት ሁለት መልክ እንዳላቸው ጠቁመው÷ እነዚህም ለውጡን በሚገባ የተረዱ ነገር ግን ጥቅማቸው እንደሚነካባቸው የሚያስቡ እና የለውጡ ባህሪ፣ አካሄድና ዓላማ ያልገባቸው አካላት ናቸው ብለዋል።

ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ ሁልጊዜ የሠላም አማራጮች ክፍት መሆናቸውንና መፍትሔ የሚገኘውም በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌዴራል ተቋማት አመራሮች ብልጽግናን ለማረጋገጥ በባለቤትነት ስሜት እና በጽናት መንቀሳቀስ አለባቸው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ÷ የሁሉምና ለሁሉም መሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ተጨባጭ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.