45ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 45ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ከእኩለ ቀን ጀምሮ በሰርቢያ ቤልግሬድ ይካዳል፡፡
በውድድሩ ከ51 ሀገራት የተውጣጡ ከ45 በላይ አትሌቶች÷ በወጣቶች እና በአዋቂ በአምስት የውድድር ዘርፎች ይሳተፋሉ፡፡
በዚሁ መሠረት 6 ሠዓት ከ 35 ደቂቃ ላይ በሚካሄደው የ8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች የሩጫ ውድድር አትሌት አቤል በቀለ፣ ሰውመሆን አንተነህ፣ ይስማው ድሉ፣ ሀጎስ ኢዮብ፣ መዝገቡ ስሜ እና ጀንበሩ ሲሳይ ይሳተፋሉ፡፡
እንዲሁም 8፡00 ሠዓት ከ45 ደቂቃ ላይ በሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የአዋቂ ሴቶች የሩጫ ውድድር÷ የ41ኛው የጃን ሜዳ ሀገር አቋራጭ አሸናፊ አትሌት ግርማዊት ገብረ እግዚአብሔር እና የ2017 እና 2018 የአምስተርዳም ማራቶን አሸናፊ አትሌት ታደለች በቀለ ይጠበቃሉ፡፡
በዚሁ ውድድር አትሌት መብሪት ግደይ፣ መሠረት ጎላ፣ በቀለች ተኩ እና ብርቱካን ወልዴ ይሳተፋሉ፡፡
በሌላ በኩል 9 ሠዓት 30 ላይ በሚካሄደው የአዋቂ ወንዶች የ10 ኩሎ ሜትር የሩጫ ውድድር÷ በአውስትራሊያ ባትረስ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አትሌት በሪሁ አረጋዊ ከኡጋንዳውያን አትሌቶች ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋል።
እንዲሁም በዚሁ ርቀት አትሌት ጭምዴሣ ደበሌ፣ ቦኪ ድሪባ፣ ጌታቸው ማስረሻ፣ ታደሠ ወርቁ እና ብርሃኑ ፀጉ ይሳተፋሉ፡፡
12 ሀገራት ብቻ በሚካፈሉበት የድብልቅ ሪሌ ወንዶች ውድድር÷ አትሌት ሀጎስ ገብረ ሕይወት፣ ተሬሳ ቶሎሳ የሚሳተፉ ሲሆን በዚሁ ዘርፍ በሴቶች አትሌት ሕይወት መሐሪ እና ብእሪ አበራ ይካፈላሉ።
በአዋቂ አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች የውድድር ዘርፎች በግል ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ከ30 ሺህ እስከ 3 ሺህ ዶላር እንደሚበረከትላቸው ተገልጿል፡፡
በወርቅነህ ጋሻሁን