በዚህ አመት 6 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ይመዘገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚህ አመት 6 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚመዘገብ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በምላሻቸውም በዚህ አመት 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ መታቀዱን ጠቅሰው፥ ነገር ግን ኮሮና ባስከተለው ተፅዕኖ ሳቢያ 6 በመቶ እድገት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ባለፉት 10 ወራት በሁሉም ዘርፍ አበረታች እድገት ሲመዘገብ መቆየቱን አስታውሰው፥ ከኮቪድ-19 ምክንያት ባለፉት ሶስት ወራት እድገቱ መቀዛቀዝ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
ኮቪድ-19 በርካታ ችግሮችን ቢያስከትልም የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በዚህ ሂደት አለመጎዳቱን አንስተዋል።
በዚህ ሂደት 138 ቢሊየን ብር ብድር መመለሱን እንዲሁም 221 ቢሊየን ብር ብድር በባንኮች መሰጠቱን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም 87 ቢሊየን ብር በባንኮች መቆጠቡን ጠቅሰው፥ በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ እድገት መታየቱን ነው ያመለከቱት።
ከተበላሸ ብድር ጋር በተያያዘም አሁን ላይ የግል ባንኮች የተበላሸ ብድር 3 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም የንግድ ባንክ ወደ 2 በመቶ ቀንሷል ነው ያሉት፤ ይህም በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን በመጥቀስ።
በማብራሪያቸው መንግሥት ከግል ባንኮች ቦንድ ማስቀረቱ፣ ብሄራዊ ባንክ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ ለባንኮች 48 ቢሊየን ብር ፈሰስ ማድረጉ፣ አነስኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች እንዳይጎዱና ብድር እንዳይስተጓጎል መደረጉ፣ ከፍተኛ ዕዳ ለነበረባቸው ግብር ከፋዮች ከ78 ቢሊየን ብር ያላነሰ እዳ መሰረዙ የሃገሪቱን ምጣኔ ሀብት መታደጉን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 10 ወራት ወደ ውጭ የሚላክ ምርት በ13 በመቶ ማደጉን ጠቅሰው፥ ቡና 667 ሚሊየን ዶላር፣ አበባ 440 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ስጋ 45 ሚሊየን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ዓለም ላይ ባስከተለው ተፅዕኖ ሳቢያ የፍላጎት መጨመርና የተፈጠረው የአቅርቦት እጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።
ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት 10 ወራት የ27 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ብሄራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓልም ነው ያሉት በማብራሪያቸው።
ከኮሮና ቫይረስ ዓለም ላይ መከሰት በኋላ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባው ነዳጅ መቀነሱን እና ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪን መቀነሱንም ነው የገለጹት።
እንደ መድሃኒት እና ማዳበሪያ ያሉ አቅርቦቶች ግን ወደ ሃገር ውስጥ እየገቡ ነው ብለዋል፤ አሁን ላይ በኮቪድ-19 ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ በተለይም አገልግሎት ዘርፉ መጎዳቱን አስታውቀዋል።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ በቱሪዝም ዘርፍ በተለይም የቱሪስት መስህብ የሆኑና በኪነ ጥበብ የተዋቡ የከተማ ፓርኮች ልማት እየተከናወነ መሆኑን አውስተው ከኮሮና ማግስት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
ከመሰረታዊ ሸቀጦች ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም መንግስት በ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ዘይትን ጨምሮ ግዥ መፈጸሙን እና ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ በምግብ ባንክ በኩል ማሰባሰብ ተችሏልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በግብርናው ዘርፍም ሰፊ የማዳበሪያ እና የማሳ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፥ የተጀመረውን ኩታ ገጠም እርሻ ማሳደግ፣ በአነስተኛ ማሳ ላይ በስፋት ማምረት፣ በቆላማ አካባቢዎች የተጀመረውን ሰፋፊ እርሻ ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የማዳበሪያ ስርጭት መደረጉን እንዲሁም የምርጥ ዘር እና የአረም ተባይና ኬሚካል ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
በጣና ሐይቅ ላይ እየተስፋፋ ካለው የእምቦጭ አረም ጋር በተያያዘ መንግስት ከአውሮፓ የተሻለ ማሽን በ300 ሚሊየን ብር ለመግዛት ድርድር ላይ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጣና ሐይቅን መታደግ ካልተቻለ ሌሎች ፕሮጀክቶችም አደጋ ይገጥማቸዋል ነው ያሉት በሰጡት ማብራሪያ።
እምቦጭን በጊዜያዊነት በሰው ኃይልና በማሽን ማስወገድ እንደሚቻል አመላክተው፥ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የበርካታ ወንዞች መፍለቂያ የሆነው የጉና ተራራ አካባቢን ማልማት እንደሚገባም ነው የገለጹት።
በተጨማሪም በርብ እና ጉማራ ወንዞች ከፎገራ አካባቢ ካለው እርሻ ወደ ሐይቁ የሚገባውን የእምቦጭ አረም ምግብ ማስቀረት እንደሚገባም መክረዋል።
ጣና ሐይቅ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውኃ ምንጭ በመሆኑ ጣና ሐይቅን መታደግ ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል።
ምርጫውን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም ኮቪድ19 በገባበት ሰሞን ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው እንዲካሄድ ፍላጎት እንደነበረው ጠቁመው፥ በዚህ ሳቢያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ጫን ባለ መልኩ እንዳናገሯቸው አስታውሰዋል።
ይሁን እንጅ ዋና ሰብሳቢዋ በሰው ጫና ሳይሆን ስራቸውን ባመኑበት መንገድ በመከወን መወሰናቸውን አውስተው ውሳኔው ትክክለኛ እንደነበር መገንዘባቸውንም ነው የተናገሩት።
ምርጫው ቢደረግ ፍላጎት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምርጫ ተብሎ ከፍ ያለ ዋጋ የሚያስከፍል አካሄድ መከተል እንደማይገባ አንስተዋል።
የሕዳሴው ግድብ መደራደሪያ ሆኗል፤ ተሸጧል እየተባለ ነው በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም፥ ሃሳቡ ከተሳሳተ አመለካከት የመጣና አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የግድቡ ግንባታ መዘግየት ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መዘግየቱ ሃገሪቱን በርካታ ጥቅሞች ማሳጣቱን አስታውሰዋል።
ግድቡ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በእኩልነት የሚጠቅ በመሆኑም ለሁላችንም ዕድገት ወሳኝነት ያለው እንደመሆኑም በበጎ ዕይታ መመልከት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ ጀምሮ የዲፕሎማሲው ስራ ጠንካራ ፈተና ገጥሞት አያውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር፥ ስራው ሲጠነክር የዲፕሎማሲው ፈተና መክበዱን አስረድተዋል።
የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ በመከወኑም በዘንድሮው ክረምት 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜትርክ ኪዩብ ውሃ እንደሚይዝ አስታውቀው፥ ከድርድሩ ጋር በተያያዘ እየሰሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ምስጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
ከሱዳን ጋር በተያያዘም ሱዳናውያን የኢትዮጵያውያን ወንድምና ወዳጅ መሆናቸውን አንስተዋል።
የሰሞኑ ከድንበር ጋር በተያያዘ የነበረውም ክስተት ሙሉ በሙሉ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ እንደሚፈታ አረጋግጠዋል
አምኒስቲ በቅርቡ ካወጣው ሪፖርት ጋር በተያያዘም ህዝቡ የሚደረገውን የሚያውቅ በመሆኑ ብዙም የሚያስጨንቅ እንዳልሆነም አብራርተዋል።
ከትግራይ ህዝብ እና ህወሓት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄም የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ መሆኑን አንስተው፥ የትግራይ ህዝብንና ፓርቲን ቀለቅሎ መመልከት ችግር መሆኑን አስረድተዋል።
ህዝቡን በአንድ ፓርቲ ብቻ መመልከቱ አግባብ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በክልሉ ውስጥ አረናን የመሳሰሉ ሌሎች ፓርቲዎች መኖራቸውን ለማሳያነት ጠቅሰዋል።
በህወሓት ውስጥም ለሃገር የሰሩና መስዋዕትነት የከፈሉ እንዳሉና በተቃራኒውም ጥፋተኛ እና ወንጀለኛ መኖራቸውንም እናምናለንም ነው ያሉት፤ አንድ ሰው ሲወቀስ የትግራይ ህዝብ የተወቀሰ አድርጎ መውሰድ ስህተት መሆኑን በማስታወስ።
ከለውጡ በኋላም የትግራይ በጀት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን በመጥቀስም መንግስት በክልሉ ለሚካሄዱ ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ ማድረጉን አመላክተዋል።
ለዚህም የትግራይ ክልል ዘንድሮ የማዳበሪያ ገንዘብ የለኝም በማለቱ ሳቢያ ስራው መቆም ስለሌለበት አርሶ አደሩ እንዳይጎዳ መንግስት 445 ሚሊየን ብር ተበድሮ ድጋፍ ማድረጉም በማሳየነት ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባለፈም የመቐለ የውሃ ፕሮጀክት፣ ለመቐለ ወልዲያ ሃራ ገበያ የባበቡር ፕሮጀክት መንግስት ያደረገውን ድጋፍ እና እየተከናወኑ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶችንም ገልጸዋል።
የታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በተመለከተም መንግስት ለጉዳዩ መልስ ለመስጠት ስራዎች መስራቱን አስረድተዋል፤ እስካሁን የሞተ ተማሪ ዜና እንዳልደረሳቸው በመጥቀስም በጠለፋው ላይ ኃላፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩንም አመላክተዋል።
እስካሁንም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ መንግስት የደረሰበትን ለህዝብ ይፋ ያደርጋል ብለዋል።
ጉዳዩ ውስብስብና መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የታለመ ከክልል ክልል እንቅስቃሴ የሚደረግበት ግለሰቦችና ቡድኖችም የተሳተፉበት ነውም ብለዋል በምላሻቸው።
በምናለ ብርሃኑ