በአግባቡ የሕክምና ክትትል ካልተደረገለት እስከ ሞት የሚያደርሰው የቲቢ በሽታ …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቲቢ ተላላፊ እና ቀስ በቀስ እያደገ የሚሄድ ሲሆን ድንገተኛና አጣዳፊ ከሚባሉት የበሽታ ዓይነቶች እንደሚመደብ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የቲቢ በሽታ 80 በመቶ ሳንባን የሚያጠቃ ቢሆንም ሌሎችንም የሰውነት ክፍሎችን ሊያጠቃ እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በሽታው የሚጠቃውን የአካል ክፍል መነሻ በማድረግም የሳንባ ቲቢ እና ከሳንባ ውጭ የሆነ የቲቢ በሽታ በመባል ለሁለት እንደሚከፈል ያብራራሉ፡፡
የበሽታው መንስኤ ምነድን ነው?
• በዓይን የማይታይ ረቂቅ ተኅዋስያን ወይም ጀርም የበሽታው መንስኤ መሆናቸውን ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡
ለቲቢ በሽታ የሚጋለጡት እነማን ናቸው?
• እንደባለሙያዎች ማብራሪያ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያጠቃል፤ በተለይም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት፣ አረጋዊያን፣ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች እና የቲቢ በሽታ አምጪ ተኅዋስያን በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ የሚኖሩ ሰዎች ተጋላጭ ናቸው፡፡
ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩት ምንድን ናቸው?
• በቂና የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት፣ በቂ የዓየር ዝውውር በሌለው ክፍል ተፋፍጎ መኖር፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ ስኳር፣ ካንሰርና ሌሎች በሽታዎች መያዝ ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥ ይገለጻል፡፡
ለምሳሌ÷ አንድ ሰው ቀድሞ በኤች አይ ቪ ከተያዘ ቫይረሱ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ስለሚያዳክም በቀላሉ በቲቢ ሊያዝ እንደሚችል ነው ባለሙያዎች የሚያስረዱት፡፡
በሽታው ከአንዱ ወደ ሌላ ሰው እንዴት ይተላለፋል?
• በሽታው በዋናነት የሚተላለፈው ታማሚው ሲስል፣ ሲያስነጥስ፣ ሲያወራ÷ የበሽታው አምጪ ጀርም ከታማሚው ሳንባ ወጥቶ በቀጥታ በትንፋሽ ወይም በዓየር አማካይነት ወደ ሌላ ሰው የመተንፈሻ አካል ሲገባ መሆኑንም ነው ባለሙያዎች የሚያብራሩት፡፡
በተጨማሪም አልፎ አልፎ “ማይኮባክቴሪየም ቦቪስ ” በተሰኘ ጀርም አማካኝነት በበሽታው ከተያዙ የቤት እንስሳት የሚገኝ ወተት ሳይፈላ ከተጠጣ ወደ ሰው ሊተላለፍ እንሚችል ይገልጻሉ፡፡
የበሽታው ምልክቶች
• ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ የቆየ ሳል (ሳሉ አክታ ያለውና ደም የቀላቀለ ወይም ያልቀላቀለ ወይም ደረቅ ሊሆን ይችላል)፣ በደረት አካባቢ የውጋት ስሜት መኖር፣ መጠነኛ ትኩሳት፣ በመኝታ ጊዜ ማላብ፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስና የሰውነት መድከም የሚሉት ከምልክቶቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ባለሙያወች ይጠቅሳሉ፡፡
ሕክምናው
• ቲቢ በአግባቡ የሕክምና ክትትል በማድረግና በባለሙያ የሚሰጡ መድኃኒቶችን በመውሰድ የሚድን በሽታ መሆኑን የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡
• የቲቢ በሽታ ምርመራም ሆነ ሕክምና በመንግሥታዊና ሕክምናውን እንዲሰጡ በተፈቀደላቸው የግል ጤና ተቋማት በነፃ የሚገኝ ሲሆን÷ የበሽታው ምልክት ሲታይም ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡