ውሃን ለመቆጠብ፣ ጥራቱን ለማሳደግና አቅርቦቱን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ውሃን ለመቆጠብ፣ ጥራቱን ለማሳደግና አቅርቦቱን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
በየዓመቱ በፈረንጆቹ መጋቢት 22 የሚከበረው የዓለም የውሃ ቀን “ውሃ ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል፡፡
የዓለም የውሃ ቀን፤ ተሟጋቾች የንፁህ መጠጥ ውሃ ጠቀሜታና ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ አፅንዖት ሰጥተው የሚሞግቱበት ዓለም አቀፍ ሁነት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ውሃ ለመኖር አስፈላጊ ቢሆንም በዓለም ዙሪያ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ንፁህ የመጠጥ ውሃ አያገኙም ተብሏል።
የዓለም የውሃ ቀን ከውሃ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤን ለማሳደግ እና የዓለምን የውሃ ችግር ለመፍታት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማበረታታት የታሰበ መሆኑም ተጠቁሟል።
ግለሰቦች፣ ማህበረሰቦች እና መንግስታት ውሃን ለመቆጠብ፣ የውሃ ጥራትን ለማሳደግ እና ለሁሉም እኩል አቅርቦትን ለማረጋገጥ እርምጃ እንዲወስዱም እንደሚያበረታታ ነው የተመላከተው።
የቻይና የውሃ ሚኒስትር ዡ ዴዢ የዓለም የውሃ ቀንን ስናከብር በህይወታችን የውሃን አስፈላጊነት እና ሀብቱን የመጠበቅን ጠቀሜታን ልናስብ ይገባል ብለዋል።
ውሃን ለመጠበቅ፣ ውሃን በዘላቂነት ለማስፋፋት እና ሁሉም ሰው ንጹህ ውሃ እንዲያገኝ በጋራ በመስራት ለሁሉም ጤናማ፣ እኩል ተደራሽነት እና ዘላቂነት ያለው መፃኢ ህይወት መፍጠር ይቻላል ማለታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።