Fana: At a Speed of Life!

ሀሰተኛ የሜዲካል ቦርድ ሰነድ በማዘጋጀት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በመፈጸም ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የሜዲካል ቦርድ ሰነድ በማዘጋጀት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሲፈፅም የተገኘን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ጌቱ ደጀን ወልደአረጋይ የተባለ የጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ሠራተኛ ወደ ውጭ ሀገር በሕገ-ወጥ መንገድ ለሚሰደዱ ዜጎች በህመም ምክንያት ከሀገር ውጭ ሄደው እንዲታከሙ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቦርድ ወስኗል የሚል ሀሰተኛ የሜዲካል ቦርድ ሰነድ በማዘጋጀት ወንጀል ሲፈፅም በቁጥጥር ሥር መዋሉን ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

ተጠርጣሪው በተጨማሪም ስለቦርዱ ውሳኔ ትክክለኛነት ከኤምባሲው የይጣራ ጥያቄ ሲቀርብም የትክክለኛነት ማረጋገጫ በመስጠት እና ለባንኮች የውጭ ምንዛሬ ሀሰተኛ የድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ ሕገ ወጥ የገንዘብ እና የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሲፈጽም እንደነበረ የተደረሰበት መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪው በሀሰተኛ ስም ዶ/ር አባይ ገብረስላሴ በመባል የሚጠራ ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ሀገራት የመሄድ ፍላጎት ያላቸውን ግለሰቦች በማፈላለግ ይህንን የወንጀል ድርጊት በመፈጸም ተጠርጥሮ ከመጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑ ተገልጽል።

በተጠርጣሪው ቢሮ ውስጥ ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ተጠርጣሪው ያዘጋጃቸው ሀሰተኛ፦
1. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ክብ ማህተም፣
2. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋክሊቲ ክብ ማህተም፣
3. የጤና ሣይንስ ኮሌጅ የሥነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና መከታተያ ክፍል ክብ ማህተም፣
4. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ክብ ማህተም፣
5. የጤና ሚኒስቴር ክብ ማህተም፣
6. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀዶ ጥገና መድሀኒት ዲፓርትመንት ክብ ማህተም፣
7. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራዲዮቴራፒ ሕክምና ማዕከል ክብ ማህተም፣
8. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ፋካልቲ የጥቁር አንበሣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ክብ ማህተም፣
9. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና የመድሃኒት እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ክብ ማህተም፣
10. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአጥንት ቀዶ ህክምና ትምህርት ክፍል ክብ ማህተም፣
11. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ኬዝ ቲም 11 ክብ ማኅተም፣
12. በጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የዜጎች ጤና ለሀገር ብልፅግና የሚል ክብ ማህተም፣
13. HILINA TADESSE TIYO (MD) Medical service General Directorate Director General የሚል ቲተር፣
በተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የተዘጋጁ የራስጌ ማህተሞች በኤግዚቢትነት ተይዘዋል ተብሏል።
በተጨማሪም÷ ተጠርጣሪው ያዘጋጃቸው የጥቁር አንበሣ ሆስፒታል የህክምና ቦርድ የታካሚዎች ሀሰተኛ ሰነዶች፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓለም አቀፍ ባንኮች ግንኙነት መምሪያ የተዘጋጁ ሀሰተኛ ሰነዶች እና የተለያዩ የግለሰቦች ፓስፖርት እና ሌሎች የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶች በተደረገው ብርበራ የተገኙ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.