Fana: At a Speed of Life!

ካፍ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ላይ እንዲከናወኑ ያስቀመጣቸው ሥራዎች ተጠናቀቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት መመዘኛ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ እንዲከናወኑ ያስቀመጣቸው ሥራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የስፖርት ፋሲሊቲ ልማትና አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አስማረ ግዛው÷ ካፍ ባስቀመጠው መመዘኛ መሰረት የስታዲየሙ እድሳትና ጥገና ስራ መከናወን ከጀመረ ከ2 ዓመት በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰዋል።

በዚህም በመጀመሪያ ዙር እድሳት የስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ፣ የተፈጥሮ ሳር ንጣፍ፣ የተመልካች መጸዳጃ ቤት፣ የተጫዋቾች የመልበሻ ክፍልና የዳኞች የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕክምና ማዕከል ግንባታ መካሄዱን አመልክተዋል።

በሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ የተመልካቾች መቀመጫ፣ የመገናኛ ብዙሃን የሥራ ክፍል፣ የመብራቶች (ፓውዛዎች) እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ስክሪን የመትከል፣ የክብርና ልዩ ክብር እንግዶች ፋሲሊቲዎች እንዲሁም ዘመናዊ የስታዲየም ውሃ ማጠጫ ስርዓት የመዘርጋት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የምዕራፍ ሁለት እድሳት ከ97 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰው÷ ቀሪ ሥራዎች በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።

ከእግር ኳስ ጋር ከተያያዙ የእድሳት ስራዎች በተጨማሪ ነባሩን የአትሌቲክስ መሮጫ መም የመቀየር ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ መሙን ለመተካት የአስፋልትና የጠረጋ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውንና አጠቃላይ የመሮጫ ትራክ እድሳት በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለዋል።

በፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅት በስታዲየሙ ይጀመራል ነው ያሉት።

በተያያዘም በምዕራፍ ሶስት የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የበይነ መረብ የቲኬት ሽያጭና በቴክኖሎጂ የታገዘ የደህንነት ስርዓት መዘርጋትን ጨምሮ ሌሎች በስታዲየሙና ዙሪያው ያሉ የውጫዊ ገጽታ ስራዎች እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ስራዎቹን ለማከናወን የሚያስችል ጨረታ በቅርቡ እንደሚወጣ የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው÷ የግንባታውን ከሶስት እስከ አራት ወራት ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ መታሰቡን አመልክተዋል።

ካፍ በምዕራፍ አንድና ሁለት የስታዲየሙ እድሳት መሟላት አለባቸው ያላቸው ስራዎች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

ካፍ በሁለት ዙር ከሰጣቸው ምክረ ሀሳቦች በተጨማሪ በምዕራፍ ሶስት ከስታዲየሙ ውጪ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች በካፍ መመዘኛዎች መሰረት ይገነባሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ እድሳት 47 ሚሊየን ብር እንዲሁም ለሁለተኛው ምዕራፍ 190 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን አመልክተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ወይም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የተቆጣጣሪ ቡድን የስታዲየሙ እድሳት ስራ ለመገምገም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.