የሃማስ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በእስራኤል ጦር መግደሉን አሜሪካ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጦር የሃማስ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ማርዋ ኢሳን መግደሉን የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን አረጋግጠዋል፡፡
ወታደራዊ መሪው የተገደለው እስራኤል ኑዜይራት በተባለ አካባቢ በፈፀመችው የአየር ድብደባ መሆኑን ባለስልጣኑ አያይዘው ገልፀዋል፡፡
ኢሳን ኢላማ ያደረገው ጥቃትም በጋዛ ሰርጥ ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ እራኤል ካደረገቻቸው ዘመቻዎች ዋነኛው መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ መጋቢት 11፣ በእስራኤል መከላከያ ኃይል እና በደህንነት አገልግሎት መካከል የተደረገው የጋራ ዘመቻ በኢሳ እና አዚዝ አቡ ታማአ በተባለ ሌላ የሃማስ አዛዥ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ተገልጿል።
ጥቃቱ ያነጣጠረው በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በሚገኝ የመሬት ውስጥ ግቢ እንደነበርም የእስራኤል ጦር ማመላከቱን ኤፍዲዲስ ሎንግ ዋር ጆርናል ዘግቧል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በፈረንጆቹ 2019 ኢሳን በልዩ ሁኔታ ከተፈረጁ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ አካቶት እንደነበር ዘገባው አያይዞ ገልጿል።