Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የራሷን አማራጭ ትወስዳለች- ፕሬዚዳንት ፑቲን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የራሷን አማራጭ ትወስዳለች ሲሉ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ፡፡

ፑቲን 87 በመቶ ድምጽ በማግኘት የሩሲያን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ በምርጫው ተሳትፎ የነበራቸውን ሩሲውያን አመስግነዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው  ነፃ፣ጠንካራና ሉዓለዊት ሩሲያን የመፍጠር ህልማቸው እውን እንዲሆን ከመላው የሩሲያ ሕዝብ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ሩሲያ በአንድ እጇ የጦር መሳሪያ በሌላኛው እጇ ደግሞ ሕዝቦቿን በማስተባበር አሁን ባለው የነባራዊ ሁኔታ የገጠማትን ችግር ተጋፍጣ ብሄራዊ ጥቅሟን ታስጠብቃለች ነው ያሉት፡፡

ከፊታችን ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷”አንድ ስንሆን ጠላቶቻችንን አሸንፈናል፣ለወደፊትም አንድ ሆነን እናሸንፋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጦርነቱን ሁኔታ አስመልከተው ባደረጉት ንግግር ÷ዩክሬን ጥይት ስትጨርስ ብቻ ሳይሆን ከልቧ የረጅም ጊዜ ትብብር ማድረግ የሚያስችል ሃሳብ ካላት ሩሲያ ለሰላም ድርድር ሁሌም ዝግጁ መሆኗን አስገንዝበዋል፡፡

በዘመናዊው ዓለም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሊፈጠር ይችላል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷አሜሪካ መራሹ ኔቶ በጦርነቱ በቀጥታ የሚሳተፍ ከሆነ 3ኛው የዓለም ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ከቀድሞ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ስታሊን በመቀጠል ሀገሪቱን ለረጅም ጊዜ መምራት የቻሉት ፑቲን የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ ውጤቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ለ5ኛ ጊዜ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው እንደሚሾሙ አር ቲ ዘግቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.