ሰሜን ኮሪያ በርካታ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ምስራቅ ባህር መተኮሷ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለባለ ብዙ ወገን የሚኒስትሮች ስብሰባ ሴኡል መግባታቸውን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ በርካታ የአጭር ርቀት ተወንጫፊ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ምስራቅ ባህር መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ ጦር ተናግሯል፡፡
ከፒዮንግያንግ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ዛሬ ንጋት ላይ የተተኮሱት ሚሳኤሎች 300 ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ምሥራቅ ባህር ላይ እንደወደቁ መመልከቱን የኃላፊዎች ጥምረት አስታውቋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ አንድ ዓይነት ኬ ኤን-24 የተሰኙ በትንሹ ሦስት የአጭር ርቀት ባላስቲክ ሚሳኤሎችን መተኮሷን የጦሩ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ ጦር ሚሳኤሎቹን ወዲያው እንዳየና እንዳረጋገጠ መረጃውን ለአሜሪካ እና ለጃፓን ባለስልጣናት ማጋራቱን ገልጿል፡፡
የኃላፊዎች ጥምረት በበኩሉ የሰሜን ኮሪያ ድርጊት በኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ግልፅና አደገኛ ጠብ አጫሪ ትንኮሳ ነው ሲል መኮነኑን አዜርኒውስ ዘግቧል፡፡