በሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሶስት ተፎካካሪዎቻቸው ጋር የተፋጠጡበት የፈረንጆቹ 2024 የሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ለቀጣይ ስድስት የስራ ዓመታት ሩሲያን ለማስተዳደር በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አራት እጩዎች እየተፎካከሩ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በስልጣን ላይ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቀኝ ክንፍ ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ሊዮኒድ ስሉትስኪ፣ የኮሚኒስት እጩ ኒኮላይ ካሪቶኖቭ እና የሊበራል ማእከላዊ አዲስ ህዝቦችን የሚወክሉት ቭላዲላቭ ዳቫንኮቭ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
በፈረንጆቹ 2020 የተካሄደውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተከትሎ በሩሲያ ውስጥ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሆነም ነው የተመላከተው፡፡
የህገ መንግስት ማሻሻያው አንድ የሀገሪቱ መሪ ሆኖ የሚያገለግል ሰው የሁለት ስድስት ዓመታት የሥልጣን ዘመን ገደብ አስቀምጧል።
በምርጫ ጣቢያዎች በአካል ከመምረጥ በተጨማሪ የ28 ግዛት ነዋሪዎች በሀገሪቱ የኤሌክትሮኒክስ ድምጽ አሰጣጥ ስርዓት በመጠቀም በኦንላይን ድምጽ መስጠት እንደሚችሉም ተገልጿል።
ምርጫው በሩሲያ የህዝብ አስተያየት ጥናትና ምርምር ማዕከል ግምት መሠረት 71 በመቶ ተሳትፎ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አርቲ ዘግቧል።
ምርጫ ጣቢያዎች በመላው ሩሲያ በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የተከፈቱ ሲሆን፤ ምርጫው ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ቀደም ብሎ ሩቅ ባሉ በርካታ የሩሲያ ግዛቶች ድምፅ የመስጠቱ መርሀ ግብር እንደተካሄደና ወደ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ድምጽ መስጠታቸውን ይፋዊ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡