ጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ ከስዊድኑ አቻቸው ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከስዊድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፈን ሎቨን ጋር ተወያዩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ለመቀበል ወደ ኦስሎ ያቀኑ ሲሆን፥ እግረ መንገዳቸውንም በስዊድን ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝታቸው ወቅትም ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፈን ለቬን ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በውይይታቸው በኢትዮጵያ እየተከናወነ ባለው የለውጥ ሂደት ላይ መምከራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።
ከዚህ ባለፈም በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ፣ ውይይት ክፍፍልን ከማስወገድ አንጻር ስለሚጫወተው ሚና፣ ስለ ቀጠናዊ መረጋጋት እንዲሁም በፖለቲካ አመራር ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማበረታታት በሚቻልበት አግባብ ላይ መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የስዊድን መንግሥት በትምህርት፣ በጤና፣ በውኃ አቅርቦት፣ በገጠር መንገድ ግንባታ እና በተቀናጀ የገጠር ልማት በኩል ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
አሁን ላይ በሃገሪቱ እየተካሄደ ካለው ለውጥ ጋር ተያይዞ ስለሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ስሜቶች በተመለከተም አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም በነገ ላይ እምነትን ስለማሳደርና እውን ይሆን ዘንድ የመስራት ጠቀሜታን በተመለከተም አውስተዋል።
የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፈን ሎቨን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል ሽልማት በማግኘታቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።
አያይዘውም የስዊድን መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እየወሰዱት ላለው የማሻሻያ እርምጃና ክንውን ያለውን አድናቆት ገልጸዋል።