የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች ለረመዳን ጾም ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች ለረመዳን ጾም ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረበ፡፡
ተኩስ አቁም ከተደረገም ከ25 ሚሊየን ለሚልቁ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚቻል ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡
በፀጥታው ምክር ቤት የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ 14 አባል ሀገራት ሲደግፉት÷ ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነቱን አለመደገፏ ተመላክቷል፡፡
ሩሲያ የውሳኔ ሐሳቡን የተቃወመችው ምክር ቤቱ የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ ግፊት ከማድረግ ይልቅ ጦርነቱን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የውሳኔ ሐሳብ ማዘጋጀት ይኖርበታል የሚል አቋም በመያዟ ነው ተብሏል፡፡
በሱዳን በተከሰተው ግጭት እስካሁን ከ8 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
እንዲሁም ከ18 ሚሊየን የሚልቁ ሱዳናውያን አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተመላክቷል፡፡