የሁቲ አማፂያን በፈፀሙት ጥቃት ሶስት መርከበኞች ተገደሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የየመን ሁቲ አማፂያን በፈፀሙት የሚሳኤል ጥቃት ሶስት መርከበኞች መገደላቸውን በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ አስታወቀ፡፡
በአማፂያኑ ጥቃት መርከበኞች ሲሞቱ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል።
ዕዙ እንዳስታወቀው÷ አማጺያኑ የባርባዶስ ሰንደቅ ዓላማን የምታውለበልብ እና “ትሩ ኮንፊደንስ” የሚል ስያሜ ባላት የጭነት መርከብ ላይ በፈፀሙት ጥቃት ሶስት ሰዎች ሲገደሉ በአራት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡
የቀሩት መርከበኞች ከመርከቧ ወርደው መሸሻቸው የተገለፀ ሲሆን የጭነት መርከቧ በተፈፀመባት ጥቃት በእሳት መያያዟን ገልጿል፡፡
አማፂያኑ በበኩላቸው÷ የሚሳኤል ጥቃቱን የፈፀሙት የጭነት መርከቧ ለባሕር ኃይል ቡድናቸው የሬዲዮ ማስጠንቀቂያ ምላሽ አለመስጠቷን ተከትሎ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው÷ የአማፂያኑ ግድየለሽ ጥቃቶች ዓለም ዓቀፋዊ የንግድ ልውውጥን ከማስተጓጎል በተጨማሪ የባህር ላይ ተጓዦችን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል ብለዋል፡፡
በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የሁቲ አማፂያን ለፍልስጤም ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት በሚል የአሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡፡
የሁቲ አማጺዎችን ጥቃት ለመከላከል በሚል አሜሪካ እና እንግሊዝ ከ40 በላይ በሚሆኑ የአማፂያኑ የጦር ሰፈሮች ላይ የተቀናጀ የአየር ጥቃት መፈፀማቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡