የአውሮፓ ህብረት ዩክሬን የጦር መሳሪያ በነጻ እንዲቀርብላት መጠበቅ የለባትም አለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን የጦር መሳሪያ በነጻ እንዲቀርብላት ልትጠብቅ እንደማይገባ የአውሮፓ ህብረት የውስጥ ገበያ ኮሚሽነር ቲዬሪ ብሬተን ገለጹ፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳስታወቁት፤ ዩክሬን አንድ ሚሊየን ከባድ የጦር መሳያዎች ከአውሮፓ ህብረት በነጻ እንዲበረከትላት ልጠብቅ አይገባም ብለዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዜለንስኪ ህብረቱ የገባውን ቃል መፈጸም አልቻለም በሚል ህብረቱ ላይ ያነሱት ቅሬታም ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ የቀረበውን ቅሬታ አጣጥለውታል።
ባለፈው ሳምንት ዜለንስኪ የአውሮፓ ኅብረት እስከ መጋቢት ድረስ ለኪየቭ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን ቦምብን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጸዋል።
ህብረቱ ማቅረብ ይጠበቅበት ከነበረው የጦር መሳሪያ መካከል 30 በመቶ ብቻ እንዳቀረበ በመግለጽ ዜለንስኪ ህብረቱ ላይ ቅሬታ ማቅረባቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የህብረቱ የውስጥ ገበያ ኮሚሽነር እንደሚሉት÷ በፕሬዚዳንት ዜለንስኪ የተገለጹት መረጃዎች ከእውነት የራቁ ናቸው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
አውሮፓ ህብረት ኬየቭን በጦር መሳሪያና በገንዘብ ለመደገፍ እቅድ አውጥቶ እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው÷ ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።
ሆኖም ግን ዩክሬን የምትፈልገውን የጦር መሳሪያ በሙሉ ህብረቱ በነጻ እንዲያቀርብላት መጠበቅ እንደሌለባት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዩክሬን የተወሰነ የጦር መሳሪያ በራሷ ልትገዛ ይገባል ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን መንግስት በወር 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ ይህንን በመጠቀም የጦር መሳሪያዎች መግዛት እንደምትችል ቲየሪ ብሬተን ማስገንዘባቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡