በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊየን በላይ ሰዎች በውፍረት እንደሚቸገሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊየን በላይ ሰዎች ከመጠን ባለፈ ውፍረት እንደሚቸገሩ ላንሴት የህክምና ጆርናል ያወጣው ጥናት አመላከተ።
ተቋሙ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ባደረገው ጥናት÷ ችግሩ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትንም እንደሚመለከትና ከአዋቂዎች ይልቅ ሕፃናትና ታዳጊዎችን ላይ በፍጥነት እያጠቃ መምጣቱን አመላክቷል።
በፈረንጆቹ መጋቢት 4 ከሚከበረው የዓለም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ቀን ቀደም ብሎ የወጣው ጥናቱ፤ በፈረንጆቹ 1990 በዓለም ላይ 226 ሚሊየን ያህል አዋቂዎች፣ ወጣቶች እና ሕጻናት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ችግር እንደነበረባቸው አስታውሷል።
ይሁንና በፈረንጆቹ 2022 አኃዙ ወደ 1 ነጥብ 38 ቢሊየን ከፍ ማለቱን ጥናቱ አመላክቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት የስነ-ምግብ ዳይሬክተር ፍራንሴስኮ ብራንካ ቁጥሩ ከተገመተው ጊዜ በፊት ከአንድ ቢሊየን በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ባለሙያዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ቢያውቁም አሁን የተመዘገበው አሃዝ በ2030 ይጠበቅ እንደነበረ አስረድተዋል።
እዚህ ግምት ላይ ለመድረስ ተመራማሪዎች ከ190 በሚበልጡ ሀገሮች ከ220 ሚሊየን በላይ ሰዎች ላይ የክብደት እና የቁመት ልኬትን ተንትነዋል ሲል ላንሴት አስረድቷል።
ጥናቱ እንዳመላከተው፤ ከፈረንጆቹ 1990 ጀምሮ በወንዶች ላይ ያለው ውፍረት በሦስት እጥፍ እና በሴቶች ደግሞ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።
በፈረንጆቹ 2022 ወደ 159 ሚሊየን የሚጠጉ ሕጻናት እና በጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ከመጠን ያለፈ ውፍረት ጋር ይኖሩ እንደነበር የጠቀሰው ጥናቱ፤ በ1990 ከነበረው በ31 ሚሊየን ጨምሯል ማለቱን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ሥር ለሰደዱ እና ውስብስብ ለሆኑ ሕመሞች የሚያጋል ነው።
ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም የመሞት እድልን ከፍ አድርጎ እንደነበር ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!