ጥፍርዎ ስለጤናዎ ምን ይላል?
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥፍር ላይ የሚታዩ ለውጦች የጤና ችግርን ሊያመለክቱ ይችላሉ።
እነዚህን ለውጦች በጥፍርዎ ላይ ከተመለከቱ ወደ ጤና ተቋማት መሄዱ ይመከራል እነሱም ፡-
1. ጥፍር ላይ ቡናማ ቀጥ ያለ መስመር
ጥፍር ላይ ቡናማ ቀጥ ያለ መስመር የሜላኖማ ምልክት ሊሆን እንደሚችል ይነገራል፤ ይህም በጣም ገዳይ የሆነው የቆዳ ካንሰር በአብዛኛው በሰውነት ቆዳ ላይ ቢታይም ምልክቱ ጥፍር ላይ ሊጀምር ይችላል::
ይህ በጣም አሳሳቢ የሚሆነው የአንድ ጣት ጥፍር ከሌላው ነጥሎ የሚጠቁር ከሆነ ነው።
2. የሚሰባበር ጥፍር
የሚሰባበር፣ ሾጣጣና የማንኪያ ቅርጽ ያለው ጥፍር የደም ማነስ ወይም የታይሮይድ በሽታን ሊያመለክት ይችላል ፤ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የጥፍር መሳሳት እንዲከሰት ያደርጋል ፤ ከፍተኛ ኬሚካሎችና ከአሴቶን-ነጻ የጥፍር ቀለም ማስለቀቅያ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ማዋል ጥፍር እንዲሰባበር ሊያደርግ ይችላል።
3. ሸንተረር
በጣት ጥፍሮች ላይ ቀጥ ያሉ መስመሮች ወይም ሸንተረር ሰዎች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ የተለመዱ ናቸው:: የቢው መስመሮች በመባል የሚታወቁት ጥልቅ አግድም ሸንተረሮች ግን ለጤና አስጊ ናቸው ::
የቢው መስመሮች የአጣዳፊ ኩላሊት በሽታ ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ትኩሳት፣ ኬሞቴራፒ፣ ከባድ ሕመም፣ ከባድ ቀዶ ህክምና፣ ደም መቀበል፣ የመኪና አደጋ ወይም ማንኛውም በሰውነት ስርዓታችን ላይ የሚደርስ ከባድ ውጥረት ምክንያትም በጥፍር ላይ ሸንተረር ሊከሰት ይችላል::
4. ቢጫ ጥፍር
ወፍራም እና ቀስ ብሎ የሚያድጉ በጣም ቢጫ ጥፍሮች ከሳንባ ችግሮች ጋር ሊዛመዱ ይችላሉ:: ቢጫ ጥፍር ሲንድረም ጥፍርዎን የሚያጠቃ ያልተለመደ በሽታ ነው። ቢጫ ጥፍር ሲንድረም ያለባቸው ሰዎች የሳንባ እና የሊምፋቲክ ስርዓት ችግር ሊሆን ይችላል።
5. ውሀ የቋጠሩ እብጠቶች
የጥፍር ማደጊያ ቆዳ ስር የሚኖሩ ትንንሽ ዉሃ የያዙ እብጠቶች ከመገጣጠሚያ ህመም ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል::
6. የጥፍር ቅርጽ ላይ ለውጦች
ሶርያሲስ የተለመደ የቆዳ በሽታ ሲሆን ፥ በአብዛኛው የሚታወቀው በቀይ ነጠብጣቦች ሲሆን ፥ በብዛት በጉልበቶች፣ በክርን እና የራስ ቆዳ ላይ ሽፍታ ያስከትላል።
ሆኖም ግን የጣት ጥፍር እና የእግር ጥፍር ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል::
የጥፍር ሶርያሲስ የተለያዩ ምልክቶች ያሉት ሲሆን ፥ ከእነዚህም ውስጥ የጥፍር መሰርጎድ ፣ ቅርጽ እና ውፍረት መለወጥ እና ጥፍር ከቆዳው ጋር መለያየት ናቸው::
በዚህም የጥፍርዎን ለውጦች በማስተዋል ወደህክምና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ስለጤናዎ ማወቅ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መረጃ ይጠቁማል፡፡