የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአረንጓዴ አሻራ ቀን መልዕክት
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ
ላለፉት ጥቂት ወራት ዓለም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ፈተና ውስጥ ገብታ ቆይታለች። የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር ሁላችንም ኃላፊነታችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን።
ይህ ጊዜ እንድናውቅ ያደረገን አንድ ነገር ቢኖር የሰውን ልጅ ተጋላጭነት፣ የግል ጤንነትን የመጠበቅ አስፈላጊነትና ጤናማ አካባቢን የመፍጠር አስፈላጊነት ነው ። ብዝኃ ሕይወትን መጠበቅና መከባከብ ቅንጦት ሳይሆን ህልውናመሆኑን አይተናል።
ልክ እንደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ኢትዮጵያም የአየር ሁኔታ ለውጥና የአካባቢ መራቆት ችግር ተጋርጦባታል። እንዲህ ዓይነት ችግሮች ለጎርፍ አደጋ ፣ ለአፈር መሸርሸር ፣ ለደን መጥፋትና ለብዝኃ ሕይወት ኪሳራ ዳርገዋታል።
የአየር ሁኔታ ለውጥን መመከትና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታዎችን ማመቻቸት የብልጽግና ጉዟችን አንዱ ጎማ ነው ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም የአካባቢ ቀንን ስናከብር ፣ በኢትዮጵያ የ2012 የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ መርሐ ግብራችንን በይፋ ጀምረናል። ከፊታችን እየመጣ ባለው የክረምት ወቅት 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታጥቀንና ቆርጠን ተነሥተናል።
ይህ ግብ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ዛፎችን ለመትከል የያዝነው ራእይ አካል ነው። ባለፈው ዓመት በጀመርነው የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ፣ በ20 ሚልዮን ወገኖች እጅ 4 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ችለናል ። በአንድ ቀን ብቻ ወደ 354 ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን በመትከል ታሪክ ቀይረናል። ከተከልናቸው መካከልም በአጠቃላይ 84 በመቶ ጸድቀዋል።
ባለፉት ወራት ለዚህ ዓመት የተከላ ወቅት ሀገር አቀፍ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል ። በመላው ሀገሪቱ የሚፈለጉትን ችግኞች በብዛት ለማዘጋጀት የተለያዩ የችግኝ ጣቢያዎች በሥራ ላይ ነበሩ።
በፌደራል እና በክልል ያሉ የመንግሥት አካላትም ዕቅዱን ለመፈጸም እንዲቻል አስቀድመው ሲያስተባብሩ ቆይተዋል።
በዚህ ዓመት ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ ተደቅኖብናል። ብዙ ነገሮቻችንን ፈትኗል። እንደ ቀድሞው ሆ ብለን አንድ ላይ እየዘመርን አንወጣም። ግን አረንጓዴ አሻራችንን አንተውም።
ርቀታችንን ጠብቀን፣ በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ፣ ከንክኪና ትፍፍግ ርቀን አረንጓዴ አሻራ እናሳርፋለን።
የዓለም የአካባቢ ቀንን ስናከብር ፣ ከኮቪድ 19 በኋላ የተሻለች ዓለም የሚመኝ ሁሉ አረንጓዴ አሻራ ለማሳረፍ አብሮ እንዲነሣ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
እንጠንቀቅ፤ ጤናችንን እንጠብቅ፤ ራሳችንን ከኮሮና ምድራችንን ከአየር መዛባት እንታደግ።