በልጆችና አዋቂዎች ከሚከሰት የኩላሊት ህመም ምልክቶች ምን ያህሉን ያውቃሉ?
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩላሊት ህመም በልጆች እና በአዋቂዎች እንደሚከሰት እና ምልክቶቹም የተለያዩ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
እንደባለሙያዎች ገለጻም በአብዛኛው የኩላሊት ህመም ምልክት ላያሳይ ቢችልም÷ እንደህሙማኑ ሁኔታ የተለያየ ምልክት አልፎ አልፎ ሊስተዋል ይችላል፡፡
የኩላሊት ህመም በልጆች ላይ ሲከሰት ከሚስተዋሉ ምልክቶች መካከልም÷ የቁመት ማጠር እና የእግር አጥንት ቀጥ አለማለት እንደሚጠቀሱ ያነሳሉ፡፡
በአዋቂዎች ዘንድ ከሚስተዋሉት ምልክቶች ደግሞ÷ የፊት እብጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የደም ማነስ፣ የድካም ስሜት፣ መለስተኛ የጀርባ ህመም፣ አጠቃላይ የሰውነት ህመም፣ የእግር ማሳከክ እና ህመም ይጠቀሳሉ፡፡
• የፊት እብጠት
ብዙ ጊዜ የፊት፣ የሆድ እና የእግር እብጠት፣ በተለይም ማለዳ ላይ ጎልቶ የሚታይ ከዐይን ሽፋን በታች የሚከሰት እብጠት (የፔሪኦሮቢታል እብጠት) የሚሉት የኩላሊት ህመም ምልክት እንደሚሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡
• የምግብ ፍላጎት መቀነስ
ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ በአፍ ውስጥ ያልተለመደ ጣዕም መኖር ከኩላሊት ህመም ምልክቶች መካከል መሆናቸውን ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡
• ከፍተኛ የደም ግፊት
አብዛኛውን ጊዜ የኩላሊት ህመም ያለባቸው ሰዎች የደም ግፊት እንደሚራቸው የሚገልጹት ባለሙያዎች÷ የደም ግፊት ከ30 ዓመት በታች ከተገኘ ወይም በምርመራ ወቅት በጣም ከፍተኛ ከሆነ ምክንያቱ የኩላሊት ህመም ሊሆን እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡
• የደም ማነስ እና የድካም ስሜት
ደም ማነስ ያለበት ሰው ከተለመደው በተለየ ሁኔታ ቶሎ የመድከም ስሜት፣ የትኩረት ማነስ እና የቆዳ መገርጣት ምልክቶች እንደሚታዩበትም ያነሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ምልክቶች አንዳንድ ጊዜ ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ምልክት መሆናቸውንም ነው ባለሙያዎች የሚያስረዱት፡፡
በተጨማሪም መለስተኛ የጀርባ ህመም፣ አጠቃላይ የሰውነት ህመም፣ የእግር ማሳከክ እና ህመም በኩላሊት ህመም ጊዜ በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ ምልክቶች መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
በአብዛኛው ከሚታዩ ምልክቶች መካከልም÷ የሽንት መጠን መቀነስ፣ በሚሸኑበት ወቅት የሚያቃጥል ስሜት መኖር፣ ቶሎ ቶሎ መሽናት (ያልተለመደ ድግግሞሽ)፣ ደም ወይም ያልተለመደ ፈሳሽ በሽንት ውስጥ ማየት እና የሽንት ቧንቧ ህመም የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ከላይ የተዘረዘሩ ምልክቶች ሲስተዋሉም ሐኪም ማማከርና ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡