የልጆች ሌሊት ላይ የሽንት አለመቆጣጠር ችግር መንስዔዎችና መፍትሄዎቻቸው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አብዛኞቹ ህፃናት 5 ዓመት ሲሆናቸው ሌሊት ላይ ሽንታቸውን መቆጣጠር ይችላሉ፡፡
ሆኖም ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት እስከ ሠባት ዓመታቸው ድረስ እንደሚቸገሩ እና በዚህም ሌሊት ሽንት ሊያመልጣቸው እንደሚችል ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ይህ ችግር ያለባቸው ሕፃናት እድሜያቸው በ 1 ዓመት በጨመረ ቁጥር ችግሩ በ15 በመቶ እየቀነሰ ይሄድና እድሜያቸው 15 ዓመት ሲሞላ 99 በመቶ ህፃናት ከዚህ ዓይነቱ ችግር ሙሉ ለሙሉ ነፃ እንደሚሆኑም ነው የሚነሳው፡፡
ሆኖም አንድ ሕጻን ሥድስት ዓመት እና ከዚያ በላይ ሆኖ ሽንትን ለመቆጣጠር ካልቻለ ወላጆች ሐኪም ማማከር አለባቸው፡፡
ሽንትን ሌሊት ያለመቆጣጠር ችግር መንስኤው ምንድነው?
1. ጥልቅ የሆነ እንቅልፍና የሽንት ፊኛ ከመጠን በላይ ሲወጠር መንቃት አለመቻል፣
2. የጉሮሮ መጥበብ ፣ ትንፋሽ መቆራረጥ እና ማንኮራፋት፣
3. በቤተሰብ ተመሳሳይ ችግር ካለ (በተለይ እናት እና አባት ላይ በልጅነታ ቸው አጋጥሞቸው ከሆነ)፣
4. የሆርሞን መዛባት በተለይ ‘‘የቫሶፕሬሲን’’ ሆርሞን ማታ ላይ በአግባቡ የማይመረት ከሆነ ፣
5. የሽንት ፊኛ ተገቢውን የሽንት መጠን መያዝ ወይም መሸከም አለመቻል (በነርቭ ችግር ወይም የአፈጣጠር ችግር ምክንያት)፣
6. የአዕምሮ ጭንቀት፣
7. አስቸጋሪና አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ እና ይህን ተከትሎ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ፍርሃት፣
8. አሰቃቂ አካላዊ ድብደባና ቅጣት፣
9. ወሲባዊ ጥቃት፣
10. የነርቭ ዘንግ ችግሮች፣
11. ከፍተኛ የሽንት መጠን ማምረት (በስኳር ፣ በኩላሊት ችግሮች ወይም በሌሎች ምክንያቶች)
12. ረጅም ጊዜ የቆየ ሆድ ድርቀት እና
13. የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በዚህም ወላጆች ፥ ልጆች ሆነ ብለው አስበውና አቅደው ወይም በእነርሱ ግድ የለሽነትና ሥንፍና የሚመጣ ችግር እንዳልሆነ ሊረዱ እንደሚገባ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡
መሰል ችግር ያለባቸውን ህፃናት ማሸማቀቅ፣ ማናደድ እንዲሁም በሰው ፊት ʺሌሊት አልጋ ላይ ሸንቷል!ʺ ብሎ ማሳፈር በፍፁም ተገቢ እንዳልሆነም ተጠቁሟል፡፡