በስፔን በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በሁለት አፓርታማዎች ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 15 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት አስታውቋል።
የእሳት አደጋው ካምፓናር በሚባል አካባቢ በሚገኝ ባለ 14 ወለል ሕንፃ ላይ በመቀስቀስ ከዚያም በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሌላ ሕንፃ መዛመቱም ነው የተገለጸው፡፡
የእሳት አደጋ ሰራተኞች ሰዎችን ከሕንፃዎቹ ውስጥ በማውጣት የማትረፍ ሥራ ሲሰሩ መስተዋላቸውም ተመላክቷል።
በህንፃው ላይ ተቀጣጣይ የሆኑ መሸፈኛዎች መኖራቸው እሳቱ በፍጥነት እንዲስፋፋ ማድረጉን ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ሕንፃው 138 አፓርታማዎችን የያዘና 450 ነዋሪዎች እንዳሉት የሕንፃው ሥራ አስኪያጅ መግለፃቸው ተመላክቷል።
በአደጋው ስድስት የእሳት አደጋ ሰራተኞችን እና አንድ ትንሽ ልጅን ጨምሮ 15 ሰዎች መቁሰላቸውም ተገልጿል፡፡
የአደጋውን መከሰት ተከትሎ የደረሱበት ያልታወቁ 14 ሰዎችን የማፈላለግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተነግሯል።
ምንም እንኳን ከባድ ንፋስ እሳቱን ቢያባብሰውም አደጋውን ከ20 በሚበልጡ የእሳት አደጋ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!