Fana: At a Speed of Life!

የሁቲ አማፂያን በእንግሊዝ መርከብ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈፀሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የየመን ሁቲ አማፂያን በኤደን ባህረ ሰላጤ እየቀዘፈች በነበረች የእንግሊዝ መርከብ ላይ የሚሳዔል ጥቃት መፈፀማቸውን የአማፂያኑ ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡

የአማፂያኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳር÷ በእንግሊዝ የጭነት መርከብ ላይ የተሳካ የሚሳኤል ጥቃት መፈፀማቸውንና የጭነት መርከቧ በደረሰባት ጉዳት ለመስጠም መቃረቧን ገልጿል፡፡

የመርከቧ ሰራተኞች ግን ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው አስታውቋል፡፡

ከመርከቧ ጥቃት በተጨማሪም ባለቤትነቱ የአሜሪካ የሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን በየመን ሁዳይዳህ ግዛት መትተው መጣላቸውንም ቃል አቀባዩ ገልጿል፡፡

አማፂያኑ ለፍልስጤም ያላቸውን ድጋፍ ለመግለፅ ጠላት ያሏቸውን እንግሊዝ እና አሜሪካ መርከቦችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት መሰንዘራቸውን እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ÷ ሁቲዎች ለመጀመሪ ጊዜ የውሃ ውስጥ ድሮን ለጥቃት ኢላማ ማዋላቸውን ገልፆ፤ የአሜሪካ የባህር ሀይል በወሰደው አምስት ተከታታይ ጥቃት የአማፂያኑን ክሩዝ ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ማውደሙን አስታውቋል፡፡

አማፂያኑ ጥቃት ማድረስ ከጀመሩበት ጥቅምት ወር ጀምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆኑን የገለፀው ዕዙ፤ ይህም በባህረ ሰላጤው በሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ የንግድ መርከቦች ላይ ያለውን የደህንነት ስጋት የበለጠ አባበሶታል ማለቱን ፕሬስ ቲቪ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.