Fana: At a Speed of Life!

ከሥጋ ኢንዱስትሪ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 01፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእርድ እንስሳት አቅርቦትን በዘላቂነት በማጠናከር ከሥጋ ኢንዱስትሪ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የዘርፉ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

የኤክስፖርት ቄራዎች የእርድ እንስሳት አቅርቦት ችግርና ሌሌች የዘርፉ ቁልፍ ማነቆዎችን ለመፍታት ያለመ የውይይት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ሃሺ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ በሥጋ ኢንዱስትሪው የእርድ እንስሳት አቅርቦት ላይ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው።

የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማሳለጥ የክልሉ ህዝብ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ለማስቻል ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ በበኩላቸው÷ ከሥጋና ከሥጋ ውጤቶች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ማነቆ ከሆኑ ችግሮች አንዱ የኤክስፖርት ሥጋ ማቀነባበሪያዎች የእርድ እንስሳትን በሚፈገለው ብዛት፣ ጥራትና ተወዳዳሪ ዋጋ አለማግኘት መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የእንስሳት እርባታ ሥራውን እና የእሴት ሰንሰለቱን ማዘመን እንደሚገባም ነው የገለጹት።

አቅርቦትን በዘላቂነት በማጠናከር ከሥጋ ኢንዱስትሪ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የዘርፉ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ኮንትሮባንድ፣ በገበያ ማዕከላት የተጋነነ የእንስሳት ቀረጥ እንዲሁም በየኬላው ተደጋጋሚ ክፍያ መጠየቅና እንስሳትን ማጉላላት በዋናነት ለአቅርቦት እጥረቱ የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውም በመድረኩ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.