ኢራን፣ ሩሲያና ቻይና የጋራ የባህር ሃይል ልምምድ ሊያደርጉ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን፣ ሩሲያ እና ቻይና በቀጣዩ ሳምንት የጋራ የባህር ሃይል ልምምድ እንደሚያደርጉ የኢራን ባህር ሃይል አስታውቋል፡፡
የኢራን ባህር ሃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ሻህ ራም በሰጡት መግለጫ÷የጋራ የባህር ሃይል ልምምዱ በምዕራብ እስያ አካባቢ ያለውን ጸጥታ በዘላቂነት ለማስጠበቅ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በኢራን ባህር ሃይል አዘጋጅነት የሚካሄደው ልምምዱ ኢራን አሁን ባለው የመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታ ሃብቶቿን እና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ሚናው ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ልምምዱ የኢራንን የባህር መርከቦች ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ የኢራንን የባህር ኃይል እርዳታ ለሚፈልጉ ሀገራት ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል አቅም የሚጎልበትበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በጋራ ልምምዱ ከሩሲያና ቻይና በተጨማሪ ሌሎች ሀገራት እንዲሳተፉ ግብዣ መቅረቡን ነው ዋና አዛዡ የገለጹት፡፡
ሶስቱ ሀገራት ለመጨረሻ ጊዜ የጋራ የባህር ሃይል ልምምድ ያደረጉት በፈረንጆቹ 2023 በሰሜናዊ የሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ሲሆን÷ የባህር ላይ ውንብድናን ለመከላከል በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም ሀገራቱ የዓለም አቀፍ የባህር ንግድ ደህንነት እና መረጋጋት እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው መባሉን ፕሬስ ቴቪ ዘግቧል፡፡