በቺሊ በተከሰተ ሰደድ እሳት ቢያንስ የ112 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቺሊ በተከሰተ የሰደድ እሳት አደጋ እስካሁን ቢያንስ የ112 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
በቺሊ ቫልፓራሶ በተሰኘ ግዛት በሚገኝ ደን ላይ የተከሰተውን ሰደድ እሳት ተከትሎም የአስቸኳይጊዜ አዋጅ መታወጁን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ገብርኤል ቦሪክ አስታውቀዋል፡፡
በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አብዛኛዎቹ በግዛቷ የሚገኝ የባሕር ዳርቻን ሲጎበኙ የነበሩ ሰዎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
እስካሁንም ቢያንስ 112 የሚሆኑ ሰዎች በአደጋው ለሕልፈት የተዳረጉ ሲሆን÷ ከ3 ሺህ እስከ 6 ሺህ የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶችም መውደማቸው ተገልጿል፡፡
ይህም በቺሊ ታሪክ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ የመጀመሪያው የእሳት አደጋ ሆኖ መመዝገቡን የሀገሪቱ ባለስልጣናት መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችን ለመርዳት ርብርብ እየተደረገ ሲሆን÷ የአደጋውን መንስኤ ለማወቅም ምርመራ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
የቺሊ መንግስት ዜጎች የደን ቃጠሎ ወደ ተከሰተባት ቫልፓራሶ ግዛት ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡም አሳስቧል፡፡