አሜሪካና እንግሊዝ የሁቲ አማፂያን ይገኙባቸዋል ባሏቸው 36 ቦታዎች ላይ ጥቃት ፈፀሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና እንግሊዝ የሁቲ አማጺያን ይገኚባቸዋል ባሏቸው 36 ቦታዎችን ኢላማ አድርገው የተቀናጀ ጥቃት መፈፀማቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለፀው÷ ሁለቱ ሀገራት በአየር እና በባህር ላይ ባደረጉት የማጥቃት ዘመቻ የየመን ሁቲዎቸ ይዞታ በሆኑ 36 ኢላማዎች ላይ የተሰካ ጥቃት ፈፅመዋል፡፡
ጥቃቱ የሁቲ አማፂያን በሜሪካ እና እንግሊዝ ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት ለመከላከል እና የአማፂያኑን ወታደራዊ አቅም ለማዳከም ያለመ መሆኑን ዕዙ አስታውቋል፡፡
በሰሜናዊ የመን የሚገኙት የሁቲ አማፂያን÷ በበኩላቸው አሜሪካ እና እንግሊዝ ለፈፀሙት የእብሪት ጥቃት አፀፋቸውን ይጠብቁ ሲሉ ዝተዋል፡፡
የሁቲ አማፂያን ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ያህያ ሳር÷ መሰል ጥቃቶች አማፂያኑ ፍልስጤማውያንን ከእስራኤል ወረራ ለመከላከል የሚያደርጉትን ድጋፍ ፈፅሞ አያስቆመውም ብሏል፡፡
የሁቲ አማፂያን የእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ለፍልስጤማውያን ድጋፋቸውን ለማሳየት በሚል በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ የእንግሊዝ እና የአሜሪካ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፅሙ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ጥቃቱን ለመከላከል የቀይ ባህርን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል አሜሪካ እና እንግሊዝ በሁቲ አማፂያን የጦር ይዞታዎች ላይ መጠነ ሰፊ የአየር እና የባህር ላይ ዘመቻ መክፈታቸውን አር ቲ እና ፕሬስ ቲቪ ዘግበዋል፡፡