Fana: At a Speed of Life!

የአገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም በሰባት የፌዴራል ተቋማት ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም በተመረጡ ሰባት የፌዴራል ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም ላይ የገንዘብ ሚኒስቴርና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ በአገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም ይዘት፣ በፖሊሲ፣ በመንግስት ሰራተኞች ብቃት ምዘና ማዕቀፍ እና በፖሊሲው ማስፈጸሚያ ዕቅድ ላይ ለሚኒስቴሩ አመራሮች በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የማሻሻያ ሪፎርሙ ዓላማ የተቋማትን አደረጃጀትና አሰራር በማዘመን በክህሎትና በባህሪ የበቃ የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማትን በመዘርጋት ለኅብረተሰቡ ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት የሀገርን የዕድገት እውን ማድረግ ነው ተብሏል፡፡

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ÷ ለሙከራ ትግበራው አንዱ ሆኖ የተመረጠው ሚኒስቴሩ ሪፎርሙን ማስፈጸም የሚችል የፕሮጀክት ጽ/ቤት በማደራጀት፣ ሃብት በመመደብና እቅድ በማውጣት በፍጥነት ወደ ትግበራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሀገራዊ ሪፎርሞችን መሸከም የሚችል ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የአስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማሻሻያ ሪፎርሙ የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ ለሙከራ በተመረጡ ሰባት የፌዴራል ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለጹት ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ሪፎርሙም ተቋማት አሰራራቸውን በማዘመን ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.