Fana: At a Speed of Life!

የማው ማው ንቅናቄ ከእንግሊዝ መንግስት የ2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ዶላር ካሳ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬኒያው ማው ማው ንቅናቄ እንግሊዝ በቅኝ ግዛት ለፈፀመችው ግፍ የ2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ካሳ መጠየቁ ተገለፀ፡፡

ንቅናቄው በፈረንጆቹ 1952 የተመሰረተ ሲሆን ኬንያ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በ1960 ነፃ እንድትወጣ ትግል ሲያደርግ የነበረ ነው፡፡

ንቅናቄው ኬንያ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ድምፁን ሳያሳማ ቆይቶ አሁን ላይ እንግሊዝ ኬንያን በቅኝ ግዛት በወረረችበት ወቅት ለፈፀመችው ግፍ ካሳ እንድትከፍል እየጠየቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቲ አር ቲ ወርልድ እንዳስነበበውም ቡድኑ ከሰሞኑ እንግሊዝ በኬንያውያን ላይ ለፈፀመቻቸው ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት 34 ትሪሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንድትከፍል መጠየቁ ተሰምቷል፡፡

የእንቅስቃሴ ቡድኑ እንዳስታወቀው ብሪታኒያ ኬንያን ተቆጣጥራ በቆየችባቸው ጊዜያት በማው ማው የደፈጣ ተዋጊዎች እና በሌሎች ኬንያውያን ላይ ግድያ፣ እስር እና ማሰቃየት ስትፈፅም ቆይታለች፡፡

የእንግሊዝ መንግስት ቀደም ሲል ለተፈፀሙ ጥቃቶች ይቅርታ መጠየቁን እና የተወሰነ ካሳ መክፈሉን የገለፀው የእንቅስቃሴ ቡድኑ÷ ነገር ግን ከቀድሞው የማው ማው ተዋጊዎች ሲቃይን የሚመጥን አይደለም ብሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2022 የእንግሊዝ ወታደሮች በኬንያ የፈፀሙትን ግፍ  አስመልክታ በአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ክስ መመስረቷ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.