አሜሪካ በኢራን ይደገፋሉ ባለቻቸው ሚሊሻዎች ላይ ጥቃት ፈጸመች
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በኢራቅ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እና በኢራን ይደገፋሉ ያለቻቸው ሚሊሻዎች የሚጠቀሙባቸው ሶስት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች።
ጥቃቱ የካታይብ ሂዝቦላህ ሚሊሻ ቡድን እና ሌሎች ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ተናግረዋል።
እርምጃው በኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች በአሜሪካ እና አጋሮቿ ላይ ለሚሰነዘሩት ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ነው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ኢራቅ የአየር ማረፊያ ላይ በተፈፀመ የሚሳኤል ጥቃት በርካታ የአሜሪካ ወታደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸውም አንስተዋል።
በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች የአሜሪካ ወታደሮችን የሚያስተናግደውን የአል አሳድ አየር ማረፊያ በባሊስቲክ ሚሳኤሎች እና ሮኬቶች ኢላማ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የዋሽንግተን የቅርብ ምስራቅ ፖሊሲ ተቋም÷ ቡድኑ በፈረንጆቹ 2023 መገባደጃ ላይ ብቅ ያለ እና በኢራቅ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በርካታ የኢራን አጋር የሆኑ የታጠቁ ቡድኖችን ያቀፈ መሆኑን ገልጿል።
በቅርብ ሳምንታትም ቡድኑ በአሜሪካ ወታደራዊ ሃይሎች ላይ ሌሎች ጥቃቶችን ፈፅሟል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
አሜሪካ በኢራን ይደገፋሉ ባለቻቸው ሚሊሻዎች ላይ በወሰደችው ጥቃት የደረሰው ጉዳት መጠንም በዘገባው አልተጠቀሰም፡፡