ጋና አሰልጣኝ ክሪስ ሁተንን አሰናበተች
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጋና በአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ አለማለፏን ተከትሎ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኙን ክሪስ ሂውተንን አሰናብታለች፡፡
ጋና በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የሻምፒዮናነት ግምት ከተሰጣቸው አራት ቡድኖች አንዷ ብትሆንም ሳትጠበቅ የምድብ ተሰናባች ሀገር ሆናለች፡፡
የበርካታ ከዋከብቶች ስብስብ የሆነችው የጋና ከሞዛምቢክ እና ግብፅ ጋር አቻ በኬፕ ቬርዴ ደግሞ ተሸንፋ ከምድብ 2 ነጥቦችን ብቻ በመያዝ ከውድድሩ ውጭ ሆናለቸ፡፡
የጋናን ደካማ የአፍሪካ ዋንጫ ውጤት ተከትሎም የጋና የእግር ኳስ ማህበር አሰልጣኝ ክሪስ ሂውተንን ከሃላፊነት ያነሳ ሲሆን÷የቡድኑ የቴክኒክ ክፍል ሃላፊዎች መሰናበታቸውም ተገልጿል፡፡
የእግር ኳስ ማህበሩ የጥቁር ከዋክብቶችን የወደፊት እጣ ፋንታ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እና የእቅድ ፍኖተ ካርታ ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል፡፡
የቀድሞ የኒውካስትል እና የብራይተን አሰልጣኝ የነበሩት ክሪስ ሂውተን የቀድሞውን የጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኦቶ አዶን በመተካት በፈረንጀቹ የካቲት 2022 ብሄራዊ ቡድኑን መቀበላቸው የሚታወስ ነው፡፡