የህፃናት የጆሮ ኢንፌክሽን ምንነት፣ መንስኤ እና ምልክቶች
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህፃናት የጆሮ ኢንፌክሽን በባክቴሪያና ቫይረስ የሚመጣ በመካከለኛው የጆሮ ክፍል የሚከሰት ህመም ነው፡፡
የህጻናት ስቴሻሊስት ዶክተር ቃልኪዳን ቤዛ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ፥ የህፃናት የጆሮ ኢንፌክሽን ህመም ከሥድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ያሉ ህጻናትን በተደጋጋሚ ያጠቃል፡፡
በዚህም ህመሙ ጆሮ ማሳከክ፣ ትኩሳት፣ ምግብ አለመመገብ፣ መነጫነጭ፣ ማስታወክ፣ የጆሮ መቅላት ከዚያም አልፎ ጆሮ አላስፈላጊ ፈሳሽ አስከትሎ የታምቡር መበሳት ድረስ ሊደርስ እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡
ይህ በሚከሰት ጊዜም የጆሮ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
የህጻናት የጆሮ ኢንፌክሽን በአፋጣኝ ካልታከመ ለተጨማሪ የጤና እክል ለአብነትም የመስማት አቅምን ሊያሳጣ እንደሚችልም ይናገራሉ፡፡
በተለይም ኤች አይ ቪ ፣ የስኳር ህመም ፣ የቫይታሚን ዲ እና ኢ እጥረት ያለባቸው፣ ጡጦ ለብዙ ሰዓት የሚጠቀሙ ህጻናት በቀላሉ የጆሮ ኢንፌክሽን ተጠቂ ናቸውም ብለዋል፡፡
በጉንፋን እና በመሰል ኢንፌክሽን ሲያዙ በቀላሉ ወደጆሯቸው የመራባት እድሉ ከፍተኛ እንደሆነም ነው ዶክተር ቃልኪዳን የተናገሩት፡፡
ወደ ጆሮ ከተራባ በኋላም ለባክቴሪያና ቫይረስ አመቺ ቦታ ስለሆነ በቀላሉ ኢንፌክሽን እንደሚፈጥርም ነው የተገለጸው፡፡
ይህ መካከለኛው የጆሮ ክፍልም ለአንጎል በጣም ቅርብ እንደሆነ አንስተው ፥ አንጎልና ጆሮን የሚከልለው አንድ ስስ አጥንት ብቻ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
ይህም በወቅቱ ካልታከመ ማጅራት ገትር፣ አንጎል ላይ አላስፈላጊ ፈሳሽ ሊፈጠር ይችላል፣ አንጎል ውስጥ ውሃ መቋጠር እንዲሁም የጆሮ ታምቡር መበሳት በማምጣት በመጨረሻም የጆሮ መስማት አለመቻልን ሊያከትል እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
መከላከያ መንገዶችም በመጀመሪያ ሥድስት ወራት ህጻናትን ጡት ብቻ ማጥባት፣ ሥድስት ወር ከሆናቸው በኋላም ተጨማሪ ምግብ በሚያስጀምሩበት ጊዜ ጡጦን እንደአማራጭ ባይጠቀሙ መክርዋል(በማንኪያ፣ በመመገቢያ ሰሃኖችና በኩባያዎች መመገብ)፡፡
እንዲሁም ጡጦ የግድ ከሆነ ደግሞ ንህፅናውን መጠበቅ ያስፈልጋል፤ጉንፋንና ተላላፊ በሽታዎች እንዲሁም የቫይታሚን ዲ እና ኢ እጥረት እንዳይኖር መጠንቀቅ (ከተከሰተም በአፋጣኝ ህክምና መውሰድ) ያስፈልጋል ሲሉ መክረዋል፡፡