የጊኒ ብሔራዊ ቡድን ማሸነፉን ተከትሎ ደስታቸውን በአደባባይ ሲገልፁ የነበሩ 6 ደጋፊዎች ህይወታቸው አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ዋንጫ ጊኒ ጋምቢያን ማሸነፏን ተከትሎ ደስታቸውን በአደባባይ ሲገልፁ የነበሩ ስድስት ደጋፊዎች ህይዎታቸው ማለፉ ተገለፀ፡፡
ክስተቱን ተከትሎም የሀገሪቱ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የቀድሞው የጊኒ ኮከብ ተጫዋች ፓስካል ፊንዶኖ ደጋፊዎች እንዲረጋጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ 15 ጊዜ መሳተፍ የቻለችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጊኒ ጋምቢያን 1 ለ 0 ያሸነፈች ሲሆን በሀገሪቱ የአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለመጀምሪያ ጊዜ ከምድብ 4 ነጥቦችን በመያዝ ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሳለች፡፡
ውጤቱን ተከትሎም ደጋፊዎች በጊኒ መዲና ኮናክሪ እና በተለያዩ ከተሞች ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም ደስታቸውን እየገለፁ ባለበት ወቅት በተከሰተ የተሸከርካሪ ግጭት ስድስት ደጋፊዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡
አደጋውን ተከትሎም የጊኒ እግርኳስ ፌዴሬሽን “የእግርኳስ አላማ በውጤት መደሰት እንጂ ከልክ ባለፈ ደስታ በሚፈጠር አደጋ የእግርኳስ ቤተሰብን ማጣት እና ሀዘንን ማምጣት አይደለም” ብሏል፡፡
በመሆኑም ደጋፊዎች በአደባባይ ደስታቸውን በሚገልጹበት ወቅት እንዲጠነቀቁ እና ራሳቸውን እንዲጠብቁ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
የቀድሞው የጊኒ ኮከብ ተጫዋች ፓስካል ፊንዶኖ÷ ”በአፍሪካው ዋንጫ አንድ ነገር እንደምናደርግ እርግጠኛ ነኝ፣ ነገር ግን ደስታችንን ከሚያሳጣን ነገር ልንጠነቀቅ ይገባል” ብሏል፡፡
የበርካታ ኮከብ ተጫዋቾች መገኛ የሆነችው ጊኒ የእግርኳስ አብዮተኛ ከሆኑ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆኗን ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል፡፡