Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ

ኢየሱስ ክርስቶስ ከልደት እስከ ዕርገት የተጓዘው ጉዞ የአዳምን ውድቀት የተከተለ ነው፡፡ አዳም በተጓዘበት የውድቀት መንገድ ተጉዞ አዳምን ከውድቀት አነሣው፡፡ ይህ ጉዞ ሁለት ዓላማ ነበረው፡፡ አንድም ለሌሎች አርአያ ምሳሌ ለመሆን ነው፡፡ አንድም ደግሞ አዳምን በየውድቀቱ ምእራፍ ለማንሣት ነው፡፡

በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀውም ለእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ነበር፡፡ ክርስቶስ እስከ ጥምቀቱ ድረስ ባደረገው ጉዞ ሐዋርያት አልነበሩትም፡፡ ያም ማለት ከ33 ዓመታት ውስጥ 30ውን ዓመት ሐዋርያት ሳይኖሩት ነው ያሳለፈው ማለት ነው፡፡ ቀደም ብለን ያነሣናቸውን ሁለቱን ዓላማዎች ሐዋርያት ከመኖራቸው በፊት ይሠራ ነበር፤ ሐዋርያት ከመጡ በኋላም ይሠራ ነበር፡፡ እስከ ዕለተ ጥምቀቱ የሠራው ሥራ በይፋ የተደረገ አልነበረም፡፡ ከጥምቀቱ በኋላ የሠራቸው ሥራዎች ግን በይፋ፣ በመገለጥ የተሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ የሁለቱ ልዩነት የዓላማና የተግባር አይደለም፡፡ በብዙ ሕዝብ በይፋ የመታወቅና ያለመታወቅ ጉዳይ እንጂ፡፡

የጥምቀትን በዓል ስናከብር ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ጉዳዮች በተጨማሪ እነዚህን ለሰው ልጆች ጉዞ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች እንድናስብ አደራ እላለሁ፡፡ እንደ ሀገር የምንሠራቸው ሥራዎች ሁለት ዓላማ ያላቸው ናቸው፡፡ ሀገርን የማዳንና ለሌሎች መንገድ የማሳየት፡፡ ኢትዮጵያ በብዙ ስብራቶች ውስጥ ያለፈች ሀገር ናት፡፡ ክርስቶስ ለአዳም እንዳዘነለት የሚያዝንላት ትፈልጋለች፡፡ ክርስቶስ ስለ አዳም ሆኖ ሸክሙን እንደተሸከመለት ሸክሟን የሚሸከምላት ትፈልጋለች፡፡

ክርስቶስ አዳምን ለማዳን ሲሠራ፣ በአዳም ላይ ተጨማሪ ቁስል ለማምጣትም የሚሠሩ ነበሩ፡፡ የበፊቱ ቁስ አልበቃቸው ብሎ፡፡ ግን ተሸንፈው ቀርተዋል፡፡ ዛሬም ሀገር ለማዳን ስንሠራ በሀገር ላይ ተጨማሪ ቁስል ለማምጣት የሚሠሩ አሉ፡፡ ተሸንፈው መቅረታቸው ግን አይቀሬ ነው፡፡ ማጥፋት ማዳንን አያሸንፈውምና፡፡

ሀገርን ለማዳን የሚሠሩ ሥራዎችን ለሁሉም ሰው በአንድ ጊዜ አይገለጡለትም፡፡ ክርስቶስ ሲወለድ ሐዋርያት አልነበሩም፤ ሲሰደድ አልነበሩም፤ ሲጠመቅ አልነበሩም፡፡ ያ ማለት ግን ክርስቶስ አዳምን የማዳን ሥራውን አልሠራም ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች ሁሉ እስኪሰበሰቡ፤ እስኪረዱና እስኪተባበሩ ከጠበቅን ሀገር የማዳን ሥራችንን መሥራት አንችልም፡፡ ነገሮች ለሁሉም የሚገለጡበት ጊዜ አለ፡፡ አስተርእዮ(መገለጥ) የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ሥራ ብቻ የሚሠራበትም ጊዜ አለ፡፡

ክርስቶስ ከልደቱ እስከ ጥምቀቱ በተጓዘ ጊዜ የኦሪቱ መሥዋዕት አልቀረም፤ የኦሪቱ የበላይነት አልተወገደም፤ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ አልተቀደደም፤ ምኩራብ አልተሻረችም፤ በሰማይና በምድር፣ በሰውና በመላእክት፣ በነፍስና በሥጋ መካከል የነበረው ጠላትነት ገና ሙሉ በሙሉ አልተሻረም፤ የሞት መውጊያ አልተሰበረም፡፡ በዚህም የተነሣ አብዛኛው ሰው ከጨለማው ዘመን እየወጣ፣ ከመከራው ዘመን እየተሻገረ፣ ከሞት ቀንበር እያመለጠ መሆኑን ገና አልተገነዘበም፡፡ ነገር ግን ቀንበሩ እየተሰበረ፣ ሞትም እየተሻረ፣ አዲስ ሕይወት እየተበሠረ፣ አዲስ መንገድም እየተጀመረ ነበር፡፡

ሀገርን ለማዳን የምንሠራቸው ሥራዎች ብርሃናቸው ቦግ ብሎ ዛሬ ላይበራ ይችላል፡፡ ለሁሉም እኩል ላይታዩ ይችላሉ፡፡ ካለፈው የችግር ጊዜ እየወጣን መሆኑ፣ ወደ አዲስ ሀገራዊ ሁኔታ እየተሻገርን መሆኑ ለጊዜው ላይታወቅ ይችላል፡፡ ከጥምቀት በኋላ ለሁሉ እንደተገለጠው፣ የኢትዮጵያ ትንሣኤና ሕዳሴ ለሁሉም ግልጽ የሚሆንት ጊዜ ይመጣል፡፡

ክርስቶስ የአዳምን የስብራት ጎዳና ተከትሎ በየወደቀበት ምእራፍ እንዳነሣው ሁሉ፤ ሀገርን የማዳን ሥራ የሀገርን የስብራት ጎዳና መከተልን ይፈልጋል፡፡ በእያንዳንዱ ምእራፍ ሀገር የወደቀችበትን እየፈለጉ ማንሣትን ይጠይቃል፡፡ ፍለጋውም፣ ጉዞውም ፈታኝ ነው፡፡

በዚህ ላይ የሄሮድስ ሰይፍ፣ የፈሪሳውያን ግብዝነት፣ የጻፎች ሤራ፣ የሮማውያን ሥጋት፣ የይሁዳ ክህደት፣ የቶማስ ጥርጣሬ፣ የአይሁድ የወሬ ዘመቻ በየአቅጣጫው አለ፡፡ ይሄም ሁሉ ሆኖ ግን መሥዋዕትነት ከፍለን ሀገራችንን እንታደጋታለን፡፡ ስብራቷን እንጠግናለን፡፡

የጥምቀት በዓል በሁለቱ ምእራፎች መካከል የሚገኝ ምእራፍ ነው፡፡ ለብዙ ሕዝብ ባልተገለጠውና በተገለጠው መካከል የሚገኝ፡፡ አስደናቂው ነገር ከ33ቱ የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ፣ ለሕዝብ ከተገለጠው ይልቅ ያልተገለጠው የአገልግሎት ዘመን መብዛቱ ነው፡፡ ሌላው አስደናቂ ነገርም ለሕዝቡ ሁሉ በተገለጠ ጊዜ እንኳን ሁሉም ሕዝብ ተረድቶ በአንድነት አለመቆሙ ነው፡፡

ይሄም የሚነግረን ታላቅ ትምህርት አለ፡፡ ትኩረታችን በዓላማችንና በዕቅዳችን ላይ መሆን እንዳለበት፡፡ አንዳንድ ነገሮች ወዲያው ግልጽ ይሆናሉ፤ አንዳንድ ነገሮች ዘግይተው ግልጽ ይሆናሉ፤ አንዳንድ ነገሮችም ከዘመናት በኋላ ግልጽ ይሆናሉ፡፡ በዓለም ላይ የመጡ ለውጦች ሁሉ የተጓዙት እንዲሁ ነው፡፡ መጀመሪያ ተቃዋሚዎቻቸው ይበዙ ነበር፡፡ የሻማውም ብርሃን ጥቂት ነበር፡፡ ሲውል ሲያድር ግን ጨለማው እየተገፈፈ፤ ብርሃኑ እየተቀጣጠለ ሄዶ፣ ለሁላችንም ደረሰ፡፡

ዛሬ ሁላችንም እንደዋዛ የምንጠቀመበት ስልክ ከመቶ ዓመታት በፊት ወደ ሀገራችን ሲገባ ብዙ ፈተና ነበረው፡፡ ተወግዞ ነበር፤ ሰይጣን ነው ተብሎ ነበር፡፡ ብዙ ተወርቶበት ነበር፡፡ በአጭር እንዲቀጭ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበርም፡፡ ያ ሁሉ ሲያልፍ ግን ዛሬ በእያንዳንዳችን ቤት ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዳችን ኪስ ገብቷል፡፡

ሀገር የማዳንም ተግባር እንደዚሁ ነው፡፡ ነገሩ በዛሬው ሚዛን አይመዘንም፡፡ በዛሬ ድጋፍና ተቃውሞ አይለካም፡፡ በዛሬ ወሬና አሉባልታ አይገመገምም፡፡ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ዛሬ የጥምቀት በዓል በሀገራችን ከ20ሺ በላይ በሆኑ ቦታዎች፣ በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ ወጥቶ ያከብረዋል፡፡ ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል፡፡ ከ2000 ዓመታት በፊት ክርስቶስ ሲጠመቅ ግን በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡

ብዙም የተወራለት፣ ብዙም የተነገረለት አልነበረም፡፡ በዙሪያው በነበሩ ከተሞች የሚኖሩ ብዙ ሰዎችም ምን እየተከናወነ እንደሆነ አልተረዱም ነበር፡፡ ጥቂቶች ብቻ በዕለቱ የተደረገውን ተአምር አይተው ክርስቶስን ተከትለውታል፡፡ ይሄው ነበር ታሪኩ፡፡

የጀመርነው ጉዞ ጥቂት የሚመስል ግን የሚበዛ፤ እዚህ የተወጠነ ግን ረዥም፤ ጥቂቶች የተረዱት፣ ነገ ግን ሕዝብ ሁሉ የሚከተለው፤ ሀገር የሚታደግና ስብራት የሚጠግን ጉዞ ነው፡፡ እዚህና እዚያ የጀመርናቸው ውጥኖች አንዱ ዓላማቸው ለሌሎች መንገድ ማሳየት ነው፡፡ ስብራት እየጠገንን፣ ሀገር እየታደግን፣መንገድም እየከፈትን መጓዛችንን እንቀጥላለን፡፡ ጅማሬው ታናሽ ቢሆንም፣ ፍጻሜው ታላቅ ስለሚሆን፤ ከጥምቀቱ የተማርነው ይሄንን ነውና፡፡

መልካም የከተራና የጥምቀት በዓል ይሁን፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥር 10፣ 2016 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.