Fana: At a Speed of Life!

ፓኪስታን በኢራን ግዛት ውስጥ ይገኛሉ ባለቻቸው አሸባሪዎቸ ላይ የአየር ጥቃት መፈፀሟን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፓኪስታን በደቡባዊ ኢራን ይገኛሉ ባለቻቸው አሸባሪዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈፀሟን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ጥቃቱ ኢራን በትላንትናው እለት የፓኪስታንን የአየር ክልል በመጣስ በጃይሽ አል አድሊ አሸባሪዎች ላይ ፈፀምኩት ላለችው የአየር ጥቃት አፀፋ ስለመሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

የኢስላማባድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር÷ የፓኪስታን ጦር በባሎችስታን የኢራን ግዛት ውስጥ በሚገኙ አሸባሪዎች ላይ የተሳካ የአየር ጥቃት መፈፀሙን ገልፆ፣ በጥቃቱ በርካታ አሸባሪዎች ተገድለዋል ብሏል፡፡

ኢስላማባድ ህዝቦቿን ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንደምትወስድም ነው የገለፀው፡፡

የኢራን ባለስልጣናት በበኩላቸው በሲሰታን-ኦ ባሎቺስታን በተፈፀመው የአየር ጥቃት 7 ኢራናውያን ያልሆኑ ሴቶች እና ህፃናት መገደላቸውን አስታውቋል፡፡

ፓኪስታን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢራን ለባሎቺስታን ተገንጣይ ቡድኖች እና ታጣቂ ቡድኖች መደበቂያ ሆናለች በሚል ስትከስ የቆየች ሲሆን ቴህራንም በኢስላማባድ ላይ ተመሳሳይ ክስ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡

የሁለቱ ሀገራት የአየር ጥቃቶች በእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት ምክንያት ውጥረት ውስጥ የገባውን የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና የበለጠ እንዳያባብሰው ተሰግቷል መባሉን አር ቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.